የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዙከርበርግ የግል መረጃ መበርበሩ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2010(ኤፍቢሲ) የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በካንብሪጅ አናላቲካ የፌስቡክ መረጃዎቹ እንደተበረበሩበት አስታወቀ።
በዚህም መረጃዎቻቸው ከተበረበሩባቸው 87 ሚሊየን ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

ይህንም ለሁለተኛ ቀን በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርቦ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ በሰጠበት ወቅት ነው የተናገረው።

አና ኢሾ የተባለች የምክር ቤቱ አባል ዙከርበርግን የበርካቶች የፊስቡክ መረጃ በካንብሪጅ አናላቲካ ሲበረበር የእንተ መረጃ ተበርብሯል ወይ ብላ ላነሳችለት ጥያቄ ፥ “አዎ” የሚል ምላሽ በመስጠት ግላዊ መረጃው እንደተበረበረበት አረጋግጧል።

እንዲሁም የግለሰቦችን መረጃ ለመጠበቅ የፌስቡክን አካሄድ ልትቀይር ትችላለህ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም የተረጋገጠ ምላሽ ሳይሰጥ እንዳለፈ ታውቋል።

ይህ የማርክ ዙከርበርግ የግል መረጃዎች መበርበርም ዜና ከተሰማ በኋላ በድርጅቱ ላይ ሌላ ጥያቄን አስነስቷል ተብሏል።

እንዲሁም በምን አይነት መንገድ የዙከርበርግ የግል መረጃ እንደተበረበረ ማወቅ እንዳልተቻልም ተገልጿል።

ምንጭ፦ፎስባይት

ተተርጉሞ የተጫነው፦ በኤፍሬም ምትኩ