ፌስቡክ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ላይ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌስቡክ መስራች እና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ ሩሲያ ድርጅቱን ለመበርበር የምታደርገውን ሙከራ ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱን አስታወቀ።

ይህንም በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርቦ የ87 ሚሊየን ሰዎች የፌስቡክ መረጃ ብርበራን በተመለከተ ንግግር ባደረገበት ወቅት ነው ያስታወቀው።

ከሩሲያ ጋር ያለውን ጉዳይም የጦር እሽቅድድም ብሎ የገለፀው ሲሆን፥ ይህንንም ለማስተካከል አበረታች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ሩሲያ በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች የሚል ጉዳይ መነሳቱን ተከትሎ በሮበርት ሙለር ተቋም ፌስቡክ ምርመራ እንደተካሄደበት አስታውቋል።

የፌስቡክንና የሌሎች በይነ መረቦችን ለመበርበር እና ለማጥቃት ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት በሩሲያ ይገኛሉም ብሏል።

በአሜሪካ ምርጫ የአማካሪነት ሚና ከነበራቸው ተቋማት ጋር ግልፅና ሚስጥራዊነቱን የጠበቀ ሂደት እንደነበረው ለምክር ቤቱ አባላት ተናግሯል።

የግለሰቦች መረጃዎችን ለመጠበቅና ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፆችን መለየት የሚያስችል መሳሪያ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነም ነው የጠቆመው።

እንዲሁም የግለሰቦችን መረጃ መጠበቅ የሚያስችሉ ደንቦች ከተዘጋጁ በዛ መሰረት ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን ዙከርበርግ አስታወቋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መተግበሪያዎች የግለሰቦችን መረጃ እንዳይበረብሩ ከማድረግ አንፃር እርግጠኛ መሆን አይቻልም ብሏል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ተተርጉሞ የተጫነው፦ በኤፍሬም ምትኩ