አፕል ቴሌግራምን የህፃናት መብትን የሚጋፉ ይዘቶች እየተንሸራሸሩበት ነው በሚል ከመተግበሪያ ዝርዝሮቹ ሰረዘው

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አፕል ኩባንያ አሁን ላይ በበርካቶች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ የመጣውን የማህበራዊ ትስስር ገፅ ከመተግበሪያዎች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱን ገለፀ።

በኩባንያው የመተግበርያዎች ክምችት ሥራ አስኪያጅ ፊል ሺሌር እንዳሉት፥ ቴሌግራም ተጠቃሚዎቹ የህፃናት የወሲብ ምስሎችን ሲቀባበሉ ማግኘቱን አስታውቋል።

አፕል ይህንንም በማረጋገጥ ቴሌግራምን ከመተግበሪያ ዝርዝሮቹ ውስጥ ማስወጣቱን እና ለሚመለከተው የቴሌግራም የስራ ሀላፊዎች ማሳወቁን ነው የገለፀው።

እነዚህ ዓይነት ህገወጥ ድርጊቶች እንዳይደገሙም የቁጥጥር ስራውን ማጠናከሩን ገልጿል።

ቴሌግራም መሰል ወሲብ ቀስቃሽ ይዘቶችን እና ፅንፈኛ ይዘቶች ሲዘዋወሩበት በቸልታ ይመለከታል በሚል የሚከሱት በርካቶች ናቸው።

በተለይም ተከታዮች ሚስጥራዊ ቡድን መስርተው በመቆለፍ የተለያዩ መልዕክቶችን እንዲጋሩ የሚፈቅድ ነው።

አፍጋኒስታን ታሊባንን የመሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ፅንፈኛ መረጃዎችን ሊለዋወጡበት ይችላሉ ብላ በመስጋት በሀገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውል አድርጋለች።

በቅርቡም የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ቴሌግራምን ወንጀለኞች የተደበቁበት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ብለውታል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ