ዴል ኩባንያ ራሱን ለቪ ኤም ዋር ለመሸጥ እያሰበ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴል የኮምፒውተር አምራች ኩባንያ ራሱን ቪ ኤም ዋር ለሚባለው የኩባንያው ቅርንጫፍ ለመሸጥ እቅድ መያዙ ተገለፀ።

ዴል በአሜሪካ ኮምፒውተሮችን፣ ሰርቨሮችን እና የኮምፒውተር መለዋወጫዎችን የሚያመርት እና የሚጠግን ኩባንያ ነው።

ቪ ኤም ዋር በበኩሉ በካሊፎርንያ ፓሎ አልቶ መቀመጫውን ያደረገ የዴል ቴክኖሎጂዎች እህት ሲሆን፥ ዴል ራሱን ለቪ ኤም ዋር ለመሸጥ እቅድ ከያዘ በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁና ያልተለመደ ስምምነት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ዴል በአሁኑ ወቅት 55 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው የቪ ኤም ዋር ኩባንያ 80 በመቶ ባለቤት እና ተቆጣጣሪ ነው።

ሲ ኢን ቢ ሲ ዋቢ በማድረግ ቴክወርም ድረገፅ እንደዘገበው፥ በአንድ ወቅት የግል የሆነው ዴል የቴክኖሎጂ ኩባንያን ከቪ ኤም ዋር ጋር ለመዋሃድ ሲል ነው የሚሸጠው ተብሏል።

ይህም መሆኑ የዴል ባለአከሲዮኖች በስቶክ ማርኬት ድርሻቸውን በቀላሉ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል።

በሽያጩም ዴል 50 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዕዳውን ለመክፈል ያስችለዋል ነው የተባለው።

የዴል እና የቪ ኤም ዋር ቃል አቀባዮች ሪፖርቱን በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሏል።