ጠንካራ እና የማይረሳ የሚስጢር ቁጥር (ፓስወርድ) እንዲኖረን የሚረዱ ምክሮች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 25፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) “የሚጠቀሙት የሚስጥር ቁጥር ጠንካራ መሆኑን እርግጠኛ ይሁኑ” የሚሉ ምክሮችን ሁሌም በተለያዩ ድረ ገጾች እንመለከታለን።

የተለመዱና በቀላሉ ሊገመቱ የሚችሉ የሚስጢር ቁጥሮችን መጠቀም ላልተገባ አደጋ ሊያጋልጠን ይችላል።

የሚስጢር ቁጥር (ፓስወርድ) በተቻለ መጠን ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያስፈልጋል። ከእኛ እና ከእኛ ወጪ ማንም ሊያውቀው ስለማያስፈልግም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጭቦችም ጠንካራ (አስተማማኝ) እና የማይረሳ ፓስዎርድ እንዴት መፍጠር እንደምንችል ያሳያሉ።
የሚስጢር ቁጥራችን

- 12 እና ከዚያ በላይ ፊደሎችን መያዝ ይኖርበታል።

- ምልክቶችን፣ ፊደሎችን እና ቁጥሮችን ሊያካትት ይገባል።

- በመዝገበ ቃላት ውስጥ የሚገኙ ቃላትን ሊይዝ አይገባውም።

በጣም የተለመዱና በዘወትር ህይወታችን ውስጥ የምንጠቀምባቸውን ቃላት ላለመርሳት ሲባል ብቻ የሚስጢር ቁጥር አድርጎ መጠቀም ሰዎች በቀላሉ አካውንታችንን ሰብረው መግባት እንዲችሉ ያደርጋል።

እነዚህን ሶስት ነጥቦች በመጠቀም ጠንካራ እና የማንዘነጋው የሚስጢር ቁጥር መፍጠር እንችላለን።

ለምሳሌ abebe desalegn የተባለ ግለሰብ abe1234 አልያም መሰል የተለመዱ የሚመስሉ የቁጥርና ፊደላት ውህድ የሚስጢር ቁጥር ከመፍጠር ይልቅ Abe&Des#23)2O የሚል ከላይ የጠቀስናቸውን ያካተተ ጠንካራ ፓስወርድ መፍጠር ይችላል።

እዚህ ላይ ግን ትልቁ ችግር የሚሆነው ለማስታወስ ከባድ መሆኑ ነው። ለዚህም መፍትሄ የሚሆነው ፓስወርዱን በተደጋጋሚ በማየት በአዕምሯችን እንዲታተም ለማድረግ ጥረት ማድረግ ነው ተብሏል።

ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ወይም በኮሌጅ ይኖሩበት የነበረው ህንጻ እና ዶርም ቁጥር B – 319 ቢሆን እና በየወሩ 200 ብር ወይም 10 ዶላር ከቤተሰብ ይላክልን እንደነበር እና በጣም የምንወዳት ፍቅረኛ ስም ማርታ ቢሆን B–319$10/Marta የሚል ጠንካራና የማይረሳ ፓስወርድ መፍጠር እንችላለን።

ፓስወርዳችንን ጠንካራ ማድረግ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል።

የሚስጢር ቁጥራችንን በተለያየ ቦታ በተደጋጋሚ የምንጠቀምበት ከሆነም ሊሰራጭና ሌሎች ሰዎች በአድራሻችን ገብተው እንዳሻቸው ሊያደርጉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።

ለዚህም ኢሜል አልያም እንደ ፌስቡክ ያሉ የተለያዩ ድረ ገጾችን ስንከፍት በሌላ ጊዜ የሚስጢር ቁጥራችንን ማስገባት ሳያስፈልገን በቀጥታ እንዲከፍትልን የሚሰጠንን አማራጭ በአሉታ ማለፍ ያስፈልጋል።

ምንም እንኳን ጠንካራ ፓስወርድ ብቻውን ከስጋት ባያድነንም የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነውና ያስቡበት።

ምንጭ:- www.howtogeek.com/