ጎግልና ኤች.ቲ.ሲ ለስማርት ስልኮች ስራ የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ስምምነት አስረዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጎግል እና ኤች.ቲ.ሲ በስማርት ስልኮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን አየሜሪካ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጎግል ከታይዋኑ ኤች.ቲ.ሲ ኩባንያ ጋር ከስምምነት የደረሰው በአውሮፓውያኑ ባሳለፍነው መስከረም ወር 2017 ሲሆን፥ አሁን ላይ ኩባንያዎቹ በስምምነቱን መፈራረማቸው ነው የተነገረው።

በስምምነቱ መሰረትም ጎግል እና ኤች.ቲ.ሲ በአዳዲስ የስማረት ስልኮች ዲዛይን ዙሪያ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል ተብሏል።

የጎግል ሀርድዌር ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ኦስቴርሎህ፥ “በኤሌክትሮኒክስ ገበያው ቀዳሚ ከሆነው ኤች.ቲ.ሲ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርመናል” ብለዋል።

“ወደፊት ጎግል እና ኤች.ቲ.ሲ በጋራ በመሆን በስማርት ስልኮች ዙሪያ አዳዲስ ፈጠራዎችን ይዘው ይመጣሉ” ሲሉም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

በስምምነቱ መሰረትም የኤች.ቲ.ሲ ባለሙያዎች ጎግልን ተቀላቅለው በጎግል ፒክስል ስማርት ስልኮች ዙሪያ የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም 2 ሺህ የሚሆኑ የኤች.ቲ ሲ ኩባንያ ኢንጂነሮችም ወደ ጎግል ኩባንያ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

ምንጭ፦ www.techworm.net