ፌስቡክ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የቢዝነስ ተቋማት የሚለቁት ይዘት የስርጭት አድማስን የሚቀንስ አካሄድ ሊከተል ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የማህበራዊ ትስስር ገፅ የሆነው ፌስቡክ ኩባንያ በገፁ ከተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን በፌስቡክ ላይ የሚሰራጩ የተለያዩ ይዘቶች ለተከታዮቻቸው በሚደርስበት መንገድ ላይ ለውጥ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

በዚህ የአካሄድ ለውጥ መሰረት ከእነዚህ አካላት ሰዎች ፌስቡክ ላይ የሚደርሳቸው የሚጫኑ ይዘቶች አነስተኛ ይሆናሉ።

በአንፃሩ በግለሰቦች እና በቤተሰቦች መካከል የሀሳብ ልውውጥ በፌስ ቡክ ላይ የሚጋብዙ ይዘቶች በተሻለ ትኩረት አግኝተው ተደራሽ እንደሚሆኑ ነው የኩባንያው መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ የተናገረው።

የማህበራዊ ትስስር ገፁን የሚጠቀሙ ሰዎች ገፁ ከተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን በሚለቀቁ ይዘቶች ተጨናንቀው የወዳጆቻቸው ወሳኝ ሁነቶች እና ኣጋጣሚዎች ሳይደርሳቸው እንደሚቀር ቅሬታ ማቅረባቸውን ነው ያስታወቀው።

ዙከርበርግ እኔና ቡድኔ ፌስቡክ ለሰዎች ደህና መሆን አጋዥ መሆኑን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለብን ብሏል።

ይህ የፌስቡክ እርምጃ ሰዎች በገፁ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እና የቆይታ ጊዜን ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቋል።

በተጨማሪም በኩባንያው ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ነው ዙከርበርግ ያመለከተው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ