በአሜሪካ ሁሉም ስራዎች በሚባል ደረጃ በቴክኖሎጂ እየታገዙ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሜሪካ ሁሉም ስራዎች በሚባል ደረጃ በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመላከተ።

ከፈረንጆቹ 2002 ወዲህ በዲጂታል መሳሪያዎች ስራዎችን የማከናወን ባህል ፈጣን ለውጥ አምጥቶ አሁን ላይ ዝቅተኛ ችሎታ የሚጠይቁ ስራዎችን ጨምሮ ከ545 ውስጥ 517 ያህሉ በቴክኖሎጂ እየታገዙ ነው ብሏል ጥናቱ።

የዋሽንግተኑ ሀሳብ አመንጪ ተቋም ብሩኪንግ የሰራው ጥናት በዚህም በርካታ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ተጠምደዋል ነው ያለው።

የቴክኖሎጂ በየጊዜው መሻሻል ቀድሞ በርካታ ሰዎች ይሰሩት የነበረውን ስራ አሁን ላይ አንድ ሰው ብቻ በዲጂታል አሰራር እንዲተገብረው ማስቻሉ ግን የሰራተኛ ቅነሳን እንዳያመጣ ስጋት መፍጠሩ ተጠቁሟል።

በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት 545 የስራ ዓይነቶች መካከል 90 በመቶው በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ናቸው።

ጥናቱ የአሜሪካ የሰራተኛ ጉዳይ ተቋም መረጃን ዋቢ አድርጎ የተሰራ ሲሆን፥ እያንዳንዱን ስራ ከሚጠቀመው በዲጂታል የሚሰራ ነው ወይስ አይደልም በሚለው መዝኗል።

በዚህም ሁሉም የስራ ዓይነቶች በ2002 ከነበሩበት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ባለፈው ዓመት በ56 በመቶ ጨምረዋል።

ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ የባለሙያ ስራዎች በየጊዜው የቴክኖሎጂ እገዛን የሚፈልጉ ሆነው ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ በ2002 ምንም ዓይነት ዲጂታላዊ አሰራር የማያስፈልጋቸው የነበሩ ዝቅተኛ ችሎታን የሚጠይቁ ስራዎች አሁን ላይ የቴክኖሎጂ እውቀትን እየጠየቁ ነው።’

የመጋዘን ሰራተኞች ከጭነት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሲሰሩ በ2002 የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ምጣኔ አምስት የነበረ ሲሆን፥ በ2016 ወደ 25 አድጓል።

በተለይም እቃዎችን በተሽከርካሪ ላይ ሲጭኑ በተሳሳተ ቦታ ማስቀመጥ አለማስቀመጣቸውን የሚያሳውቁ በርካታ ዲጅታል መሳሪያዎችን የመጠቀም ባህላቸው ማደጉ ነው የተነገረው።

ጥናቱ የቤት ጣራ መገጣጠም ስራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ ማከናወን ከነበረበት የዜሮ ምጣኔ በአንድ ጊዜ 22 ደርሷል ያለ ሲሆን፥ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ስራዎች ደግሞ ከ3 ወደ 26 አድገዋል።

አሁን ላይ በአሜሪካ ስራዎች ሁሉ በዲጂታል እየተከናወኑ መሆኑን እና ጥሩ ክፍያ ማስገኘታቸውን ደርሰንበታል ይላሉ የጥናቱ ተባባሪ አዘጋጅ ማርክ ሙሮ።

ሆኖም ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከስራቸው የመነሳት ዝቅተኛ እድል መኖሩን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠው የሶፍትዌር አበልፃጊ ሙያ ዲጂታላዊ በሆነ መንገድ ስዎችን የማከናወን ምጣኔ ከነበረበት 97 ወደ 94 ወርዷል።

ለዚህም ምክንያቱ በርካታ ሰፍትዌር የማበልፀግ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወደ ሃላፊነት በማደጋቸው እና የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ስራቸውን በመቀነሳቸው ነው ተብሏል።

 

 

 

ምንጭ፦ reuters.com