ፎርድ በእንቅልፍ ምክንያት የሚደርስ የተሽከርካሪ አደጋን የሚቀንስ ኮፍያ ሰራ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፎርድ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ በእንቅልፍ ምክንያት የሚደርስ የተሽከርካሪ አደጋን የሚቀንስ አዲስ ኮፍያ መስራቱን አስታውቋል።

ከተሽከርካሪ አደጋ መንስኤዎች ውስጥ አሽከርካሪዎች መኪና በመንዳት ላይ እያሉ የማንቀላፋት ወይም በእንቅልፍ መያዝ አንዱ ነው።

በተለይም እንዲህ አይነቱ ችግር ከባድ ተሽከርካሪዎችን በሚያሽከረክሩ ሹፌሮች ላይ በስፋት የሚስተዋል ሲሆን፥ ምክንያቱ ደግሞ ነጻ የሆነ መንገድ ላይ ለረጅም ሰዓት ያለ እረፍት ስለሚያሽከረክሩ ነው።

ታዲያ ፎርድ ኩባንያ ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ያለውን አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ ያለ ሲሆን፥ ይህም አሽከርካሪዎች በእንቅልፍ ስሜት ውስጥ ሆነው በሚነዱበት ጊዜ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው።

ኮፍያው የመቆጣጠሪያ ስርዓት የተገጠመለት ሲሆን፥ አሽከርካሪው በማሽከርከር ላይ እያለ በሚያንቀላፋበት ጊዜ ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት አሸክርካሪው መኪናውን አቁሞ እረፍት እንዲወስድ ለማድረግ የሚረዳ ነው።

ኮፍያው በፎርድ ኩባንያ ስር በሚገኘው የብራዚል የከባድ መኪናዎች ማምረቻ ፋብሪካ የተሰራ ሲሆን፥ ሰዎች ለመደበኛ አገልግሎት ከሚያደርጉት ኮፍያ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ሆኖም ግን ሰዎች በእንቅልፍ ውስጥ ሆነው መኪና እንዳያሽከረክሩ የሚረዳ መከተተያ እና መቆጣጠሪያ ቁሶች ተገጥመውለታል።

አሽከርካሪዎች መኪናቸውን በማሽከርከር ላይ እያሉ የእንቅፍል ስሜት በሚጫናቸው ጊዜ ኮፍያው እንዲነቁ አሊያም አቁመው እረፍት እንዲወስዱ የሚረዳ ሶስት አይነት ምልክቶችን እንደሚያሳያቸውም ተነግሯል።

ምልክቶቹም ንዝረት፣ ድምፅ ማሰማት እና የመብራት ምልክት መስጠት ናቸው።

ፎርድ የኮፍያውን ውጤታማነት ለማረጋገጥም ለ8 ወራት ያክል በተመረጡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ ሙከራ ማድረጉም ተነግሯል።

ሆኖም ግን ኮፍያው መቼ ለገበያ ይቀርባል በሚለው ዙሪያ ፎርድ የረጅምም ይሁን የአጭር ጊዜ እቅዱን በይፋ አላሳወቀም ነው የተባለው።

ምንጭ፦ www.cnet.com