አዲሱ አይፎን ኤክስ ስማርት ስልክ በቅዝቃዜ ምክንያት ስክሪኑ እንደማይሰራ አፕል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አፕል አዲሱ አይፎን ኤክስ ስማርት ስልኩ በቅዝቃዜ ምክንያት ተች ስክሪኑ እንደማይሰራ አረጋገጠ።

አይፎን 10(iPhone X) የተሰኘው የኩባንያው አዲሱ ስማርት ስልክ ወደ ገበያ ከቀረበ ሳምንታትን ቢያስቆጥርም ችግሮች አብረውት መጥተዋል።

ከችግሮቹ መካከልም ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ተች ስክሪኑ የተፈለገውን ስራ አለመስራቱ ዋናው ነው ተብሏል።

አይፎን 10 (iPhone X)ን ገዝተው የሚጠቀሙ አንዳንድ ደንበኞች፥ ስልኩ የአር ሁኔታ ከሞቃት ወደ ቀዝቃዛ በሚቀየርበት ጊዜ በሰከንዶች ልዩነት ተች ስክሪኑ መስራት ማቆሙን ተናግረዋል።

ለዚህም እያንዳንዱን የተች ስክሪን ቁልፎች በጣት አሻራ ለመክፈት ቢሞክሩም በቅዝቃዜው ምክንያት መስራት እንዳልቻለ ነው በማሳያነት ያቀረቡት።

ይህ ችግር ግን የሁሉም አይፎን 10 (iPhone X) ስማርት ስልኮች ችግር አይደለም፤ አንዳንዶቹ በተገቢው ሁኔታ ይሰራሉ ተብሏል።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ስልኩን ቆልፎ ወዲያውኑ በሚከፈትበት ጊዜ ስክሪኑ ወደ መደበኛ አገልግሎቱ የሚመለስበት እድልም መኖሩ ተጠቁሟል።

እያንዳንዱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ መደበኛ አገልግሎት የሚሰጥበት የራሱ የሙቀት መጠን መኖሩ ይህን ችግር አዲስ ባያደርገውም ለኩባንያው ግን አሳሳቢ መሆኑ ተነግሯል።

አሁን ላይ አፕል ችግሩን ተረድቶ በሶፍትዌር ማሻሻያ የስማርት ስልኩን ችግር ለመቅረፍ እየሰራሁ ነው ብሏል።

 

 

 

 

www.neowin.net