ቻይና የመጀመሪያውን ስማርት የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በራሱ በመጠቀም የሚሽከረከረውን ስማርት የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀች።

ፋው ጄፋንድ አውቶሞቲቭ የተባለው መኪና አምራች ኩባንያ በቻንግቹን ሸንዘን የፍጥነት መንገድ ላይ ሶስት ስማርት ተሽከርካሪዎች በራሳቸው እንዲሽከረከሩ ያደረገው ሙከራ የተሳካ መሆኑን ገልጿል።

የከባድ ጭነት ተሽከርካሪው 40 ቶን ክብደት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን፥ ለማቋረጥ፣ ለመታጠፍ እና ፍጥነት ለመጨመር የሚያስችል አውቶማቲክ ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል።

ከሰው እጅ እርዳታ ውጭ መሪን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ስርዓትም አለው ነው የተባለው።

የፋው ጄፋንግ አውቶሞቲቭ ኩባንያ ጄነራል ማናጀር በቴክኖሎጂ ታግዘው የሚጓዙ ስማርት ተሽከርካሪዎች፥ በቀጣይ ዓመታት አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን ተሽከርካሪዎችን እንደሚተኩ ተናግረዋል።

ኩባንያቸው በፈረንጆቹ 2018 ከፍተኛ ብቃት እና ጥራት ያለው ሞዴል እንደሚያመርት የገለፁ ሲሆን፥ በ2020 ደግሞ በአምስተኛ ትውልድ የኔትወርክ ተግባቦት የሚሰራ ተሽከርካሪን ያመርታል ብለዋል።

በ2025 የመጀመሪያውን አሽከርካሪ አልባ መኪና ለማምረት ማቀዱንም ነው የጠቆሙት።

ኩባንያው የመጀመሪያውን ቻይና ሰራሽ ተሽከርካሪ በ1956 ያመረተ ሲሆን፥ ከዚያ ወዲህ 6 ሚሊየን መኪናዎችን አምርቷል።

በተያዘው 2017 ባለፉት 9 ወራትም፥ 198 ሺህ መኪናዎችን በመሸጥ በቻይና ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

 

 

 

 


ምንጭ፦ news.cgtn.com