ጎግል በሩሲያ የሚደገፉ ማስታወቂያዎችን በዩ ትዩብና በጂ ሜይል ላይ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጎግል የሩሲያ ኩባንያዎች በርካታ የአሜሪካ ዶላር ወጪ በማድረግ በዩ ትዩብ፣ በጂ ሜይል እና በጎግል የማፈላለጊያ ገጽ ላይ ማስታወቂያዎችን ሲያሰራጩ እንደነበር ደርሼበታለው ብሏል።

ማስረጃዎችም ሩሲያ የኩባንያውን የማስታወቂያ ፕላትፎርም በመጠቀም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 የተካሄደው የአሜሪካ መርጫ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር እንደሞከረች የሚያረጋግጥ መሆኑም ነው የተነገረው።

ማስታወቂያዎቹ ያሰራጩት ድርጅቶች ምንም እንኳ በቀጥታ ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም አብዛኞቹ ግን በተዘዋዋሪ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን እንደደረሰበትም ጎግል አስታውቋል።

የጎግል ቃል አቀባይ በትናንትናው እለት እንደተናገሩት፥ “ጥብቅ የሆነ የማስታወጢያ ፖሊሲ አውጥተናል፤ ይህ ፖሊሲ የፖለቲካ እንዲሁም በዘር እና በሀይማኖት ላይ ጥቃት የሚፈፅሙትን የሚከላከል ነው” ብለዋል።

“በአሁኑ ጊዜ የመረጃ ስርዓታችንን ያለአግባብ የተጠቀመ አካል ላይ ከተመራማሪዎቻችን ጋር በመሆን ጠለቅ ያለ ምርመራ እያካሄድን እንገኛለን፤ ለምንሰራው ስራሰም ድጋፍ ያስፈልገናል” ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስት ኮንግረስ በሀገሪቱ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከሩሲያ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማስረጃዎች እንዲያስረክቡ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ፌስቡክም በቅርቡ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ከሩሲያ ጣልቃ ገብነት ጋር ግንኙነት ያላቸውን 3 ሺህ የፖለቲካ ማስታዎቂያዎች ለኮንግረሱ መስጠቱ ይታወሳል።

ጎግልም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 22 2017 በአሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ በሩሲያ ጣልቃ ገብነት ዙሪያ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት እና ምስክርነት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ፦ www.cnet.com