ማይክሮሶፍት የዊንዶውስ 10 ስማርት ስልክ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ስራውን አቋረጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማይክሮሶፍት የስማርት ስልኮች ዊንዶውስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ማምረት ማቆሙን አስታውቋል።

የኩባንያው የዊንዶውስ 10 ሃላፊ በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት፥ ማይክሮሶፍት ከዚህ በኋላ ለስማርት ሞባይል ስልኮች የሚሆን የዊንዲውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም መስራት ላይ ትኩረት አይሰጥም።

የዊንዶውስ 10 ሃላፊው ጆይ ቤልፊዮር፥ “እኔ ለራሴ የምጠቀመውን ስማርት ስልክ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከዊንዶውስ ወደ አንድሮይድ ቀይሬያለው” ሲሉም አስታውቀዋል።

microsoft_windows_2.jpg

ዊንዶውስ 10 የሞባይል ኦፕሬቲንግ ሲስተም ተጠቃሚዎች በቀላሉ በኮምፒውተራቸው እና በስማርት ስልኮች ላይ ተመሳሳይ መተግበሪያዎችን መጠቀም እንዲያስችሉ በማድረግ ነበር የተጠቃሚዎቹን ቀልብ ለመሳብ የታሰበው።

ሆኖም ግን የታሰበውን ያክል ስኬታማ መሆን አልቻለም ነው የተባለው።

የዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር መካከል በዓለም ገበያ ላይ ሊይዝ የቻለው ድርሻም 0 ነጥብ 03 በመቶ ብቻ መሆኑን አይ.ዲ.ሲ የተባለ የጥናት ኩባንያ አስታውቋል።

የዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተምን የሚጠቀሙ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ያስታወቀው የጥናት ኩባንያው፥ በዚህም የተነሳ በሞባይል ኔትዎርክ አቅራቢዎች እና አከፋፋዮች ዘንድ ተፈላጊነቱ የቀነሰ ነው ብሏል።

ከደንበኞች በኩል ሲታይም ኦፕሬቲንግ ሲስተሙ እንደ አንድሮይድ እና አይ.ኦ.ኤስ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ጥሩ የሆኑ አገልግሎቶችን አይሰጥም ተብሏል።

የዊንዶውስ 10 ሃላፊው ጆይ ቤልፊዮር፥ ማይክሮሶፍት የዊንዶውስ 10 ኦፕሬቲንግ ሲስተምን ማቅረብ ቢያቆምም፤ ለስማርት ስልኮች የሚሆን ኦፕሬቲንግ ሲስተም ማቅረቡን ሙሉ በሙሉ አላቋረጠም ሲሉም አብራርተዋል።

በያዝነው ዓመት ኩባንያው አንድሮሜዳ የተባለ አዲስ የዊንዶውስ 10 ስሪት እየሰራ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፥ ይህ የዊንዶውስ ስሪት በሁሉም አይነት ኮምፒውተሮች ላይ እንደሚሰራም ተነግሯል።

ይህ ኦፕሬቲንግ ሲስተም በቀጣዩ ዓመት ለገበያ እንደሚቀርብ ነው የሚጠበቀው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ