በስሎቫኪያ ብዙ ሰዎች የረሷቸው የሞባይል ስልኮችን ለዕይታ ያቀረበ ሙዚየም ተከፍቷል

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 3 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ስሎቫኪያዊው የ26 ዓመት ስቴፋን ፖልጋሪ በቀጥታ ኢንተርኔት የገበያ ባለሙያ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ደግሞ ፊቱን ወደ ሞባይል ስልክ ሙዚየም አዙሯል።

ሙዚየሙ ቆየት ካለ ጊዜ ጀምሮና አሁን ላይ እየተመረቱ ያሉ ማናቸውንም አይነት የሞባይል ስልክ ጎብኝዎች በአዕምሯቸው እንዲያስታውሱ ለማድረግና በጉብኝታቸውም የሚደሰቱበትን ሙዚየም መክፈት ነው።

ወጣቱም ከዚህ በፊት የተመረቱ ሞባይል ስልኮችን በቀጥታ የኢንተርኔት ግብይት ከየስፍራው እያሰባሰበ ይገኛል።

በዚህ ጥረቱም እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 500 ሞዴሎችን ያካተቱ 3 ሺህ 500 ስልኮችን ሰብስቧል።

ፖልጋሪ በሚኖርባት ዶብሲና ከተማ የተሰራው ሙዚየሙ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ባለፈው ዓመት ነው ተከፍቶ አግልግሎት የጀመረው።

በሞባይል ስልክ ስብስቡ ኖኪያ 3310 እና ሲመንስ ኤስ 4 ሞዴሎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በውስጡ ከሚገኙት የሞባይል ስልኮች መካከል ከ20 ዓመት በፊት ገበያ ላይ የነበረውና 23 ሺህ የስሎቫክ ኮሩና ዋጋ የሚጠይቀው ሲመንስ ኤስ 4 የተባለው ስልክም ይገኝበታል።

የስልኩ ዋጋ በስሎቫኪያ አንድ ሰው በሁለት ወር ውስጥ የሚያወጣውን ሙሉ ወጪ ይሸፍናል።

በሙዚየሙ ውስጥ ከመጀመሪያው ተች ስክሪን ስማርት ስልክ ውጭ ሌሎቹ ከብዙ ዓመት በፊት የተሰሩ ስልኮች ናቸው የሚገኙት ብሏል ፖልጋሪ።

ፖልጋሪ በአሁኑ ወቅት የሚጠቀመው ስልክ አይፎን ቢሆንም የድሮዋ ኖኪያ 350i ትበልጥብኛለች ይላል።

ሙዚየሙን የድሮ ስልኮችን ማየት የፈለጉ ሰዎች እየጎበኙት ይገኛል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦indianexpress.com