በኢኩይፋክስ ድርጅት የመረጃ መረብ ላይ በደረሰ ጥቃት 143 ሚሊየን ደንበኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2009(ኤፍ ቢ ሲ) የዱቤ ሽያጭ ስምምነቶችን የሚያስተዳድረው የኢኩይፋክስ ድርጅት የመረጃ መረብ ላይ በደረሰ ጥቃት 143 ሚሊየን አሜሪካውያን ደንበኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ድርጅቱ ገልጿል።

ኢኩይፋክስ ባወጣው መግለጫ የመረጃ መረብ ጥቃቱ የደንበኞች የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሮች፣ የልደት ቀናትና አድራሻ ላይ ያነጣጠረ ነው።

የተወሰኑ የብሪታኒያና የካናዳ ዜጎች የሆኑ የድርጅቱ ደንበኞችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ተብሏል።

ሆኖም የድርጅቱ ወሳኝ የአገልግሎትና የዱቤ ስምምነት የመረጃ መረብ ላይ ጉዳት አለመድረሱ ነው የተገለፀው።

የመረጃ መረብ ጠላፊዎች ከግንቦት ወር አጋማሽ እስከ ሃምሌ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ጥቃቱን መፈፀማቸውም ተረጋግጧል ተብሏል።

በመረጃ መረብ ጥቃቱም የ209 ሺህ ደንበኞች የዱቤ አገልግሎት ካርድ ቁጥሮችና ሌሎችም መረጃዎች ተበርበርዋል።

የመረጃ መረብ ጥቃት ሪፖርቱ በአሜሪካ ደረጃ ግዙፉ ጥቃት መሆኑም ነው የተነገረው።

ድርጅቱ ከአሜሪካ፣ ከብሪታኒያና ከካናዳ የመረጃ መረብ ደህንነትና የፋይናንስ ስርዓት ቁጥጥር ተቋማት ጋር በመሆን ለመስራት አቅዷል።

አሁን ላይም ነፃ የዱቤ አግልግሎት ክትትልና ሌቦችን የመከላከል ስራ እያከናወንኩ ነው ብሏል።

የኢኩይፋክሰ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ስሚዝ ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ጠይቀው፥ የመረጃ መረብ ጥቃቱ ደንበኞችን ስጋት ላይ የጣለብን ቢሆንም በቅርቡ ሁሉንም ነገር እናስተካክለን ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ