የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት በኢንቴል ኩባንያ ላይ የተጣለው ቅጣት እንደገና እንዲጣራ አዘዘ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት በኢንቴል ኮምፒውተር አምራች ኩባንያ ላይ የተጣለው ቅጣት እንደገና ህጋዊ ማጣራት እንዲካሄድበት አዘዘ።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ያሳለፈው ውሳኔ ህብረቱ በ2009 በኩባንያው ላይ የጣለውን የ1 ነጥብ 06 ቢሊየን ዩሮ ቅጣት እንዲመረመር የሚያዝ ነው።

ግዙፉ የዓለማችን ኮምፒውተር አምራች ኢንቴል ቅጣቱ የተጣለበት ህገወጥ የሽያጭ ዘዴን ተጠቅሟል በሚል ነው።

የአውሮፓ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ኮሚሽን ኩባንያው ህብረቱን የገበያ ውድድር ህግ በመጣስ ኤ ኤምዲ የተባለውን ኩባንያ ከገበያ ለማስወጣት ሞክሯል የሚል ውንጀላም አቅርቧል።

በዚህም የገበያ የበላይነትን ለመውሰድ ህገወጥ አካሄድን ተጠቅሟል የሚለው የህብረቱ ኮሚሽን በርካታ አውሮፓውያን የገበያ አማራጭ እንዳይኖራቸው አድርጓልም ብሏል።

የህብረቱ ፍርድ ቤትም የታችኛው ፍርድ ቤት ያሳለፈውን የኩባንያው የህግ ጥሰት ቅጣት እንደገና እንዲመረመረ የሚያዘውን ውሳኔ ደግፎ አፅድቆታል።

ኢንቴል ላለፉት ስምንት ዓመታት የአውሮፓ ህብረት የገበያ ስርዓት ቁጥጥር ተቋም ብዙ ስህተቶችን በመስራት ገበያውን ብቻውን ለመቆጣጠር ሞክሯል በሚል ቅጣት የጣለብኝ ብሏል።

ህብረቱ በበኩሉ ኢንቴል x86 የተባለውን የኮምፒውተር ምርቱን፥ አምራቾች እንዲገዙት ሲያግባባ ነበር፤ ለዚህም አዲስ የሚያመርቱትና ገበያ ላይ የሚያውሉት ኮምፒውተር ካለ እንዲያዘገዩለት ገንዘብ ከፍሏቸዋል የሚል ክስ አቅርቧል።

የአውሮፓ ህብረት ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የቅጣት ውሳኔውን በ2014 ያፀና ሲሆን አሁን ላይ በተጨማሪነት ኩባንያው የገበያ የበላይነትን ለመውሰድ የጣሳቸው መርሆዎች በድጋሚ ማጣራት እንዲደረግባቸው ወስኗል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦አሶሺየትድ ፕረስ