የብሪታኒያ ዩኒቨርሲቲዎች ለመረጃ መረብ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የመረጃ መረብ ጥቃት አድራሾች አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ማዞራቸው ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሯቸው ምርምሮች ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳቸው እያደገ መሆኑን ተከትሎ ለመረጃ መረብ ጠላፊዎች የጥቃት ኢላማ እንዳደረጋቸው እየተነገረ ነው።

በዚህ ዓመት የብሪታኒያ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም በምርምር ስራዎችና በገቢ መጠናቸው ልክ ቀዳሚውን ደረጃ ቢይዙም የመረጃ መረብ ጥቃት ፈተና ሆኖባቸዋል።

በ2017 በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የደረሰው የመረጃ መረብ ጥቃት ካለፈው ዓመት እጥፍ መሆኑም ነው የተነገረው።

እንደ ዘ ታይምስ መረጃ ከሆነ በዓለም ምርጥ ዩኒቨርሲቲ በመባል አንደኛ የሆነው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን እና የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ጨምሮ

በበርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ 1 ሺህ 152 የመረጃ መረብ ጥቃቶች ደርሰዋል።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም 515 የመረጃ መረብ ጥቃቶችን በማስተናገድ ቀዳሚው ሆኗል።

የህክምና፣ የምህንድስና እና የሚሳኤል ምርምሮች የመረጃ መረብ ጥቃት ኢላማዎች እንደነበሩም ተገልጿል።

አሁን በብሪታኒያ ዩኒቨርሲቲዎች ያጋጠመው የመረጃ መረብ ጥቃት ፈተና ለሌሎች ሀገራት ትምህርት ይሆናል ተብሏል።

የገንዘብ ተቋማትን በማሽመድመድ ላይ የሚገኘው የቫይረስ ጥቃት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማነጣጠሩ፥ የምርምር ውጤቶችን ባለቤት ለማክሰርና የጥቃት ኢላማቸውን የሚያከሽፉ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎችን ለማወቅ ያለመ ነው።

በዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ መረብ ደህንነት የምርምር ስራዎች ዳይሬክተሩ ካርሰቴን ማፕል ዩኒቨርሲቲዎች የኮምፒውተር መረብ ደህንነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መክረዋል።

 

 

 

 

 

 


ምንጭ፦www.computerweekly.com