ታዳጊ ሴቶች በሚደርስባቸው ፆታዊ ትንኮሳ ከማህበራዊ ትስስር ገፆች እየራቁ ነው - ጥናት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማህበራዊ ትስስር ገፆች ፆታዊ ትንኮሳ የሚደርስባቸው ሴት ታዳጊዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ።

ፕላን ኢንተርናሽናል ያደረገው የዳሰሳ ጥናት በርካታ ሴቶች የማህበራዊ ትስስር ገፆች ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው አሳይቷል።

በጥናቱ 1 ሺህ 2 ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 48 በመቶው በማህበራዊ ሚዲያዎች ጾታዊ ትንኮሳ ይፈፀምብናል ብለዋል።

ይህ ቁጥር ትንኮሳ ከሚደርስባቸው ወንዶች (40 በመቶ) በ8 በመቶ የበለጠ መሆኑንም ነው የሴቶች መብት ተሟጋቹ ፕላን ኢንተርናሽናል ያስታወቀው።

ሮዛ የተሰኘች የ19 አመት ታዳጊ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ትንኮሳ ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል አንዷ ናት።

ከስካይ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረገችው ሮዛ፥ “በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ጓደኞቼ በአካል ቢያገኙኝ ሊናገሩት የማይደፍሩትን ነገር በኦንላይን ይልኩልኛል” ብላለች።

የሴቶች እኩልነትን የሚሰብክ የፌስቡክ ገፅ ከፍታ በመክፈቷ ፆታዊ ትንኮሳ የደረሰባት የ15 አመት ታዳጊ አምብሪንም የተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፅ አድራሻዎቿን ለመዝጋት ተገዳለች።

ሴቶች በአለባበሳቸው እና ውበታቸው የተነሳ የተለያዩ ትንኮሳዎች እንደሚደርስባቸውም ነው የገለፀችው።

ጥናቱ ሴቶች በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚደርስባቸው ፆታዊ ትንኮሳ እያየለ ቢመጣም ከእነዚህ የመረጃ እና መገናኛ መንገዶች መራቁ መፍትሄ አይሆንም፤ ለስራ እና ማህበራዊ ግንኙነታቸው መዳበር አይነተኛ ሚና አላቸው ብሏል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች 73 በመቶ የሚሆኑት በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚደርስባቸው ትችት ለመራቅ እርምጃ እንደሚወስዱ ነው የተናገሩት።

ሉሲ ሩስዌል የተሰኙ የፕላን ኢንተርናሽናል ሰራተኛ እንደሚሉት፥ የሚፈፀሙ ትንኮሳዎች ሴቶች የስራ፣ ፖለቲካ እና መዝናኛ መድረክ ከሆኑ የማህበራዊ ትስስር ገፆች እንዲርቁ እያደረጉ ነው።

ታዳጊ ሴቶች በሚደርስባቸው ፆታዊ ትንኮሳ ተደናግጠው ከማህበራዊ ሚዲያ መራቅን አማራጭ አድርገው እንዲወስዱ አንመክርም ነው ያሉት።

ሩስዌል በርካታ ጠንካራ ሴቶች አሁንም የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ተቋቁመው በርካታ ተከታዮችን ማፍራት መቻላቸውንም አንስተዋል።

 

 

 


ምንጭ፦ http://news.sky.com/