የቻይና ዋነኛ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ዊቻት፣ ዌይቦ እና ባይዱ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾች (ዌይቦ፣ ዊቻት እና ባይዱ ቴይባ) የሳይበር ደህንነት ህጎችን ተላልፈዋል በሚል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።

የሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት ተቋም እንዳለው ሶስቱ የትስስር ገፆች የተጠቃሚዎቻቸውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አልቻሉም።

ሰዎች እነዚህን የማህበራዊ ትስስር ገፆች በመጠቀም ከሽብር ጋር የተገናኙ መረጃዎችን መቀባበላቸውንም ነው ያስታወቀው።

እነዚህ ድርጊቶችም “የሀገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ናቸው” ብሏል ተቋሙ።

ዌይቦ፣ ዊቻት እና ባይዱ ቴይባ በአለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የማህበራዊ ትስስር ገፆች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፥ እያንዳንዱ በቻይና ከ100 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚ አላቸው።

በአሁኑ ወቅት ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት የትስስር ገፆቹ ተጠቃሚዎቻቸው የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ መረጃዎችን እንዳይለዋወጡባቸው ቁጥጥር እንዲያደርጉም ተቋሙ አሳስቧል።

በሀገሪቱ ባለፈው ሀምሌ ወር የሀገሪቱን ህግ አላከበሩም በሚል 60 የአሉባልታ ማሰራጫ ናቸው የተባሉ ድረ ገፆች መዘጋታቸው ተገልጿል።

በኢንተርኔት ሳንሱር በከፍተኛ ደረጃ የምትታማው ቻይና፥ እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም ያሉ የውጭ ሀገር የማህበራዊ ትስስር ገፆችን እና መተግበሪያዎችን መዝጋቷ ይታወቃል።

እንደ ጎግል ያሉ የመረጃ ማፈላለጊያዎችም በቻይና የተዘጉ ሲሆን፥ በርካታ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ድረ ገፆችም እንዳይከፈቱ ተከልክለዋል።

እነዚህን የተከለከሉ ድረ ገፆች ለመክፈት የሚሞክሩ ሰዎችም ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ነው የተባለው።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ