ብሪታኒያ የመረጃ መረብ ጥቃትን የማይከላከሉ ተቋማትን እስከ 17 ሚሊየን ፓውንድ እንደምትቀጣ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሪታኒያ መንግስት የመረጃ መረብ ጥቃትን በራሳቸው አቅም የማይከላከሉ ተቋማትን እስከ 17 ሚሊየን ፓውንድ ለመቅጣት እንደተዘጋጀ አስታውቋል፡፡

በተለይም የትራንስፖርት፣ የጤና እና የኤሌክሪክ አገልግሎትን የሚያስተጓጉሉ የመረጃ መረብ ጥቃቶችን መከላከል በማይችሉት ላይ ቅጣቱ ከበድ እንደሚል ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም በእቅዱ ላይ የቀረበው ቅጣት ተቋማቱ የመረጃ መረብ ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉ ለማስገንዘብ የወጣ ሲሆን፥ የገንዘብ ቅጣቱ ተዘናግተው ራሳቸውን ለመረጃ ጠላፊዎች በሚያጋልጡት ላይ የሚያነጣጥር ነው ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ መንግስት የቅጣት ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀው በብሔራዊ የጤና አገልግሎት መስሪያ ቤት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነው፡፡

ጥቃቱም የመስሪያ ቤቱ ስራዎችን ያስተጓጎለ ሲሆን፥ አምቡላንሶች ስራ እንዲያቆሙ እና የህሙማን መረጃዎች በመረጃ ጠላፊዎች እንዲቆለፉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተደራጀ የመረጃ ጠላፊዎች የደረሰው ጥቃት ዋናክራይ በተሰኘ የኮምፒውተር ቫይረስ የተፈፀመ ሲሆን በመላው ዓለም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

ለአብነትም በብሪታኒያ አየር መንገድ 75 ሺህ ተጓዦች በረራ እንዲቋረጥ በማድረግ 80 ሚሊየን ፓውንድ ኪሳራ አድርሶበታል፡፡

በሀገሪቱ በ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ፓውንድ በጀት ተቋማት የመረጃ መረብ ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ የተዘጋጀውና ቅጣትን ያካተተው ስትራቴጂ በ2018 ግንቦት ወር ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፡-ዘጋርዲያን