"ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ጎግልን አይቀላቀሉም" የሚል ፅሁፍ ያወጣው የኩባንያው ሰራተኛ ከስራ ተሰናበተ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጎግል ኩባንያ ሴቶች እና ወንዶች እኩል የስራ እድል የማያገኙት አድልኦ ስለሚፈፀምባቸው ሳይሆን በስነህይወታዊ የፆታ ልዩነታቸው የተነሳ ነው የሚል ፅሁፍ ያወጣው የኩባንያው ሰራተኛ ከስራ ተሰናብቷል።

አወዛጋቢው ፅሁፍ የኩባንያውን የስነ ምግባር ህግ የጣሰ ነው ብለዋል የጎግል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱንዳር ፒቻይ።

ሰሞኑን በርካቶች የተቀባበሉት ማስታወሻ በጎግል ኩባንያ ተቀጥረው የሚሰሩት ሴቶች አነስተኛ የሆኑት በስነህይወታዊ የፆታ ልዩነት ምክንያት እንጂ ኩባንያው አድልኦ ስለሚፈፅም አይደለም ይላል።

የጎግል ዋና ስራ አስፈጻሚ ይህ ፅሁፍ በስራ ገበታ ተለምዷዊ የሆነ የጾታ ልዩነት አስተሳሰብን ያራመደ በመሆኑ የኩባንያውን ህግ ተላልፏል ብለዋል።

ሰራተኛው የፈፀመው ተግባር ሴት ሰራተኞችን እና የስራ ቦታ ባህልን የሚረብሽ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ጎግል የሰራተኞቹን የመናገር ነፃነት እንደማይገፍ የተናገሩት ስራ አስፈፃሚው፥ የግለሰቡ ድርጊት ግን ከዚህም የተሻገረ ነው ብለዋል።

ጎግል የሰራተኛውን ማንነት ይፋ ያላደረገ ሲሆን፥ ኒውዮርክ ታይምስ ግን ጀምስ ዳሞር እንደሚሰኝ እና በአሁኑ ወቅት ከስራ መሰናበቱን ዘግቧል።

የሶፍትዌር ኢንጂነር እንደሆነ የተነገረለት ጀምስ ዳሞር “የጎግል አይዲዮሎጂካል ኢኮ ቻምበር” የሚል ርዕስ በሰጠው ፅሁፉ፥ “ሴቶች እና ወንዶች በስነ ህይወታዊ ልዩነታቸው ምክንያት የተለያየ ብቃት ይኖራቸዋል፤ ይህ ልዩነታቸውም በቴክኖሎጂ ዘርፍ እና አመራርነት ከወንዶች እኩል ውክልና እንዳይኖራቸው አድርጓል” ይላል።

ዳሞር “ስነህይወታዊ የፆታ ልዩነት የሚፈጥረውን ተፅዕኖ መናገርም የፆታ እኩልነትን ካለመቀበል ጋር ማያያዝ ማቆም አለብን” ብሏል።

“ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ፈሪ በመሆናቸው ከፍተኛ ውጥረት ያለበትን ስራ አይፈልጉም” የሚል ሀሳብ ያለው ይህ ፅሁፍ የኩባንያውን በርካታ ሰራተኞች አስቆጥቷል።

አንዲት የኩባንያው ሰራተኛም በግለሰቡ ላይ እርምጃ ካልተወሰደ ስራ እንደምትለቅ በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች።

በተቃራኒው የሶፍትዌር ኢንጂነሩ ይህን ፅሁፍ ካወጣ በኋላ ከበርካታ የጎግል ሰራተኞች “ዝምታውን ሰብረህ የውስጣችን ስለተናገርክ እናመሰግናለን” የሚሉ የኢሜል መልዕክቶች እንደደረሱት ነው ብሉምበር የዘገበው።

ጎግል ሰራተኛውን ለፆታዊ እኩልነት ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ ቢልም እንደሌሎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሴቶችን በመቅጠር ረገድ አሁንም ትችት ይሰነዘርበታል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና ኒውዮርክ ታይምስ