የአይ.ቢ.ኤም ተመራማሪዎች በ1 ማግኔቲክ ቴፕ ውስጥ 330 ቴራ ባይት መረጃ በማስቀመጥ አዲስ ክርወሰን አስመዝግበዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአይ.ቢ.ኤም ተመራማሪዎች በአንድ የማግኔቲክ ቴፕ የመረጃ መያዣ ውስጥ 330 ቴራ ባይት መረጃን በማስቀመጥ አዲስ ክብረወሰን በእጃቸው አስገብተዋል።

የአይ.ቢ.ኤም ቴክኖሎጂ እና የሶኒ ኩባንያ በጋራ በመሆን በአንድ ጊዜ 330 ቴራ ባይት ወይም 330 ሺህ ጊጋ ባይት መረጃን የሚይዝ አነስተኛ ማግኔቲክ ቴፕ ሰርተዋል።

ኩባንያው ከሶኒ ጋር በመሆን የሰራው እና አዲስ ክብረ ወሰን የያዘው የመረጃ መያዣው አሁን በገበያ ላይ ካለው በ20 እጥፍ የሚበልጥ ነው ተብሏል።

የመረጃ መያዣ ማግኔቲክ ቴፑ በአንድ ስኩዌር እስከ 201 ጊጋ ባይት መረጃን የሚይዝ ሲሆን፥ አሁን በገበያ ላይ ያሉት ግን በስኩዌር ከ5 እስከ 7 ጊጋ ባይት መረጃ ነው መያዝ የሚችሉት።

አዲሱ የአይ.ቢ.ኤም የመረጃ መያዣ ማግኔቲክ ቴፕ በአንድ ጊዜ እስከ 330 ሚሊየን መፅሃፍቶችን መያዝ ከሚችለው የዓለማችን ግዙፉ ሀርድ ድራይቭ የሚበልጥ መሆኑም ተነግሯል።

በመጠኑ ደግሞ በሰው እጅ መዳፍ ውስጥ የሚያዝ ነው።

የአይ.ቢ.ኤም ተመራማሪዎች አዲሱ ፈጠራቸውን በጃፓን በተካሄደው የማግኔቲክ ሪከርዲንግ ጉባዔ ላይ ማቅረባቸውም ታውቋል።

የኩባንያው ተመራማሪዎች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ2006 ወዲህ መረጃ መያዣ ቴፖችን በመስራት የዓለም ክብረ ወሰን ሲሰብሩ ይህ ለ5ኛ ጊዜያቸው መሆኑም ተነግሯል።

የአይ.ቢ.ኤም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2015 220 ቴራ ባይት ወይም 220 ሺህ ጊጋ ባይት መረጃ መያዝ የሚችል መያዣ መስራታቸውም ይታወሳል።

ምንጭ፦ www.techworm.net