በ2017 በኢንተርኔት መረጃ ለማፈላለግ ቀዳሚ ሆነው የተገኙ አራት ብሮውዘሮች…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በኢንተርኔት መረጃዎችን ለማፈላለግ እና ድረ ገፆችን በቀላሉ ለማግኘት ምቹ ናቸው የተባሉ አራት ብሮውዘሮች ይፋ ሆነዋል።

በ2017 ምርጥ ተብለው ከተለዩት ብሮውዘሮች መካከል ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር አልተካተተም፡፡

በጣም የተሻሻሉ እና ለአጠቃቀም ቀላል ሆነው በ2017 የቀረቡት አራት ብሮውዘሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. ክሮም (Chrome)

ጉግል ክሮም በተጠቃሚዎች እና በኢንተርኔት ገበያው ቀዳሚ የሆነ ብሮውዘር ነው።

ክሮም በውስጡ በያዛቸው የመረጃ ዝርዝሮች በርካታ ደንበኞችን መሳብ የቻለ ሲሆን፥ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል ነው ተብሏል፡፡

የትርጉም ስራዎችን፣ የፒዲ ኤፍ መረጃ ወደ ተለያዩ ፎርማቶች መለወጫ፣ የመረጃ ዳራ ማስቀመጫዎችን እና ሌሎችንም የፊት ገፆች አካቶ በመያዙ ተመራጭ ሆኗል፡፡

2. ፋየርፎክስ (Firefox)

ከጉግል ሰራሹ ክሮም የተሻለ ሚስጥራዊነትን የሚያስጠበቅና በ2017 ተመራጭ ሆኖ የቀረበው የኢንተርኔት ብሮውዘር ሞዚላ ፋየርፎክስ ነው፡፡

ፋየርፎክስ ሌሎች ብራውዘሮችን አካቶ ማስጠቀም የሚያስችል "add-on" የሚል አማራጭ ማቅረቡም በደንበኞች እንዲወደድ አድርጎታል።

በተለይም ከዚህ በፊት የፈለግናቸውን መረጃዎች ሌሎች ሰዎች ከፍተው እንዳይመለከቱ ለመከልከል፥ የመዝጊያ እና የመክፈቻ ቁልፎችን መጨመሩ የመተግበሪያውን ተመራጭነት ከፍ እንዳደረገው ይታወሳል።

3. ኦፕራ (Opera)

ይህ ብሮውዘር በርካታ የክሮም ማስፈንጠሪያዎችን በጃቫስክሪፕት ቪ8 አማካይነት ለተጠቃሚዎቹ ማድረስ ይችላል።

እንደ ቱርቦ ያሉ ያልተለመዱ መለያዎችን ያካተተው ኦፕራ፥ ድረ ገፆችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እና መረጃዎችን በጊዜ ለይቶ ለማስቀመጥ ያግዛል፡፡

ተጠቃሚዎች ጉግል ዶት ኮም እና ስካም ዶት ኮም ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ስውር የመረጃ አድራሻዎቻቸውን በቀላሉ ለእነርሱ ብቻ እንዲደርሳቸው የሚያደርግ የሚስጥር መጠበቂያ ቁልፍም አለው፡፡

በቅርቡ እንደ ዋትስአፕ፣ ፌስቡክ ሜሴንጀር እና ቴሌግራም ያሉ የማህበራዊ የትስስር ገፆችን አንድ ጊዜ ብቻ በመጫን ለማግኘት የሚያስችል ማሻሻያ ተደርጎለታል፡፡

4. ማይክሮሶፍት ኤጅ (Microsoft Edge)

ማይክሮሶፍት ኤጅ የተባለው የኢንተርኔት መረጃ ማፈላለጊያ መተግበሪያ፥ አሁንም በመሻሻል ላይ የሚገኝ ሲሆን በ2017 የተሻሉ ከሚባሉት ተርታ ተመድቧል፡፡

ከሚስተዋሉበት ችግሮች ውጭ ከዊንዶውስ 10 ጋር መገናኘቱ እንዲሁም የራሱ ማስታወሻ መመዝገቢያ የተዘጋጀለት መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

የተለያዩ ድረ ገፆችን በአንድ ይዞ መገኘቱ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ መጻህፍትን ለማንበብ ምቹ መሆኑ ሌላው መልካም ጎኑ ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡- www.pcworld.com