በኢንዶኒዥያ የመታገድ ስጋት ያደረበት ቴሌግራም የሽብር ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች መሰረዝ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚስጥራዊ የመልዕክት መለዋወጫነት የሚታወቀው ቴሌግራም በኢንዶኔዥያ የሽብር ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ማስተላለፊያነት እያገለገለ ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎ ኩባንያው ለሀገሪቱ ባህል እና ቋንቋ ቅርበት ያላቸውን የይዘት አጣሪ ባለሙያዎች ቀጥሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በእስካሁኑ ስራውም የሽብር እና ፅንፈኛ አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችን የሚለዋወጡ ተጠቃሚዎቹን ከአባልነት መሰረዙን እና መልዕክታቸውን ማጥፋቱን ገልጿል፡፡

ቴሌግራም በፈረንጆቹ 2013 በፓቬል ዱሮቭ እና በወንድሙ ኒኮላይ የተፈጠረ የግል ሚስጥርን በመጠበቅ መልዕክት ለመለዋወጥ የሚያስችል መተግበሪያ ነው፡፡

ዱሮቭ ለቴሌግራም 40 ሺህ ተከታዮቹ በጻፈው መልዕክት የኢንዶኔዥያ መንግስት ጥቃትን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችን እና የሚያሰራጩትን ሰዎች እንዲሰርዝ መጠየቁን እንዳላወቀ ጠቅሶ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የኢንዶኔዥያ የኮሙዩኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ ቴሌግራም አሉታዊ ጫና ያላቸውን ይዘቶች መቆጣጠር ካልቻለ በሀገሪቱ አገልግሎት እንዳይሰጥ ሊያግደው እንደሚችል ባሳለፍነው አርብ አስታውቆ ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ በከፊል እርምጃውም የኢንተርኔት ኩባንያዎች የጥቃት አላማ ያላቸውን 11 የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ከኔትወርክ ተደራሳሽነት እንዲሰርዟቸው ጠይቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የኢንፎርማቲክስ አፕሊኬሽንስ ዳይሬክተር ጀነራሉ ሳሙኤል ፓርጌራፓን፥ መተግበሪው ኢንዶኔዥያውያን የታጣቂ ሃይሎች አባል እንዲሆኑ ጥሪ ማስተላለፊያነት፣ የጥላቻ ንግግሮች ማስተናገጃ እና የቦምብ አሰራር ማሳያ በመሆን እያገለገለ ነው ብለዋል፡፡

በኢንዶኔዥያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂ ሃይሎች በምርመራ ወቅት በሰጡት ቃል ከሌሎች የቡድናቸው አባል ጋር ግንኙነት የሚያደርጉት በቴሌግራም አማካኝነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሚወሰዱ እርምጃዎችን ትዕዛዝ ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍም ቴሌግራም በታጣቂ ቡድኖች ዋነኛ የመልዕክት ማድረሻ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት 18 ወራትም በሀገሪቱ ከሚገኘው ባህሩን ናይም እስከ ሶሪያው አይ ኤስ የሽብር ቡድን ድረስ የጥቃት ኢላማዎችን አቀነባብሮ ለማስተላለፍ መተግበሪያው ቁልፍ ሚና ሲጫወት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

ዱሮቭ የቴሌግራም ኩባንያቸው በአሁኑ ወቅት እነዚህን የጥቃት ኢላማ ያነገቡ ተጠቃሚዎችን ከኢንዶኔዥያ መንግስት በተላከለት መስፈርት መሰረት መሰረዙን አስታውቋል፡፡

የሀገሪቱ የኮሙዩኒኬሽን እና የኢንፎረሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሩዲአንታራ ከዱሮቭ ይቅርታ እንደተቀበሉ ተናግረው እየወሰደው ያለው እርምጃም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሽብር ቡድኖች ማህበራዊ የትስስር ገጾችን በመጠቀም በመላው አለም የጥቃት ኢላማቸውን እያራመዱ መሆናቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ምንጭ፡- አሶሼትድ ፕሬስ