በምታመነጨው ሃይል የምትንቀሳቀሰው ጀልባ የስድስት አመታት ጉዞዋን በፓሪስ ጀምራለች

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በምታመነጨው ሃይል የምትንቀሳቀሰውና አለም ለያዘችው የአረንጓዴ ልማት አጋዥ ናት የተባለችው ጀልባ ለስድስት አመታት የምታደርገውን ጉዞ በፓሪስ አሃዱ ብላለች።

ጀልባዋ በአየር ንብረት ለውጥ ተቆርቋሪዎች እና በአረንጓዴ ልማት ሃሳብ ደጋፊዎች አማካኝነት የተሰራች ሲሆን፥ ለሚቀጥሉት ስድስት አመታት ራሷን በራሷ ሃይል እየሞላች የባህር ላይ ቆይታዋን ታደርጋለች ተብሏል።

የመጀመሪያ ጉዞዋንም ከትናንት በስቲያ በፈረንሳይ ፓሪስ የሲየን ወንዝ አንድ ብላ ጀምራለች።

ጀልባዋ ሃይል ከፀሃይ እና ነፋስ ሃይል መንቀሳቃሻ የሚሆናትን ሃይል የሚያመነጩ መሳሪያዎች ተገጥመውላታል።

5 ነጥብ 25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የወጣባት ጀልባ ጉዞዋን ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ የምታደርግ ሲሆን፥ በቀጣዮቹ ስድስት አመታት ደግሞ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ አምባሳደር ሆና አለም ላይ የውሃ አካላትን ታዳርሳለች።

30 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት ያላት ጀልባ፥ ከጸሃይ እና ነፋስ መንጭቶ በምታገኘው ሃይል ቀጣዮቹን ስድስት አመታት በባህር ላይ ትቀዝፋለች።

ነዳጅም ሆነ ሌላ በካይ ነገር የማትጠቀመው ጀልባ፥ ከሃይድሮጂን የምታመነጨውን ሃይል በተጨማሪነት ትጠቀምበታለች።

ለዚህ የሚያገግለውና በውሃ አካል ላይ በሚለቀቅ የኤሌክትሪክ ንዝረት ሃይድሮጀን ማመንጨት የሚያስችል ቴክኖሎጅም ተገጥሞላታል።

ቴክኖሎጅው ከጀልባዋ በውሃ አካሉ ላይ በሚለቀቅ ንዝረት አማካኝነት ውሃው ላይ ከሚገኙ የተለያዩ ውህዶች ሃይድሮጅን ማመንጨት ያስችላል።

በዚህም ጀልባዋ ለመንቀሳቀስ የሚያስፈልጋትን ሃይል እንድታገኝ የሚያግዛት ይሆናል።

ጀልባዋ ቀን ቀን ከጸሃይና ነፋስ በሚገኝ ሃይል የምትንቀሳቀስ ሲሆን፥ በምሽት ወቅት ደግሞ በሃይድሮጂን ሃይል ትሰራለች።

ይህ ደግሞ አለም አሁን በጋራ ለቆመችለት የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ መርህ ማሳያና መልዕክት ማስተላለፊያ ይሆናልም እየተባለ ነው።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ phys.org/news