በመረጃ መረብ ጥቃት ሳቢያ አለም ላይ የ53 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ ይደርሳል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም ላይ እየተፈጸመ ያለው የመረጃ መረብ ደህንነት ጥቃት እስከ 53 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያስከትል ተገለጸ።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የኢንሹራንስ ተቋምና የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ሊዮድስ ኦፍ ለንደን የተባለው ድርጅት እንደገለጸው፥ የመረጃ ምዝበራው በአለም ኢኮኖሚ ላይ የ53 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ክስረት ሊያስከትል ይችላል።

ዛሬ ይፋ የሆነው የተቋሙ መረጃ በመረጃ ምዝበራው አማካኝነት በትላልቅ ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን የገንዘብ ክስረት ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

ይህ የኢኮኖሚ ክስረት ደግሞ አለም ላይ ያሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ እና የገበያ መዋዠቅ እንዲሁም ለኮምፒውተርና ፕሮግራሞች ማስተካከያ የሚወጣውን ወጪም ያካተተ ነው።

የድርጅቱ ሪፖርት የአሜሪካ መንግስት የመረጃ መረብ ጥቃቱ በኒውክሌርና በሃይል ማመንጫ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ያጠቃል የሚል ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ የወጣ ነው።

ባለፈው ወር ከዩክሬን የተነሳው የኮምፒውተር ቫይረስ፥ አለም ላይ 850 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ ማድረሱ ይነገራል።

አሁን ላይ መቋጫ ያላገኘው የመረጃ መረብ ጥቃትም ከዚህ በኋላ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ነው ያለው ድርጅቱ።

ይህ ደግሞ በአለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍ ያለ ጫናን ሊፈጥር እንደሚችልም ነው ኩባንያው የገለጸው።

አሁን ላይ ድርጅቱ በዚህ ሳቢያ የሚደርስ አማካይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ከ4 ነጥብ 6 እስከ 53 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳልም ነው ያለው።

ሊዮድስ ኦፍ ለንደን ከመረጃ መረብ ደህንነት ጋር በተያያዘ፥ አለም ላይ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ዋስትና የሚይዝ ተቋም ነው።

 

 

ምንጭ፦ ሬውተርስ