አሜሪካ ካስፐርስኪ በሃገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውል አገደች

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የሩሲያው የመረጃ መረብ ደህንነት እና አንቲ ቫይረስ ሶፍትዌር አቅራቢ የሆነው ካስፐርስኪ በሃገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዳለች።

ዋሽንግተን መቀመጫውን ሞስኮ ያደረገውና ከመረጃ መረብና ከኮምፒውተር ደህንነት ጋር የተያያዙ ሶፍትዌሮችን የሚያቀርበው ተቋም በሃገረ አሜሪካ ጥቅም ላይ እንዳይውል እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።

በዚህም የተቋሙ የሆኑ ሶፍትዌሮች በአሜሪካ ጥቅም ላይ አይውሉም፤ ካስፐርስኪም ምርቱን በአሜሪካ ምድር አያቀርብም።

ይህ ደግሞ ካስፐርስኪ በቴክኖሎጅው ዘረፍ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ ከሩሲያ የደህንነትና የስለላ ተቋማት ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ በመታመኑ ነው ተብሏል።

እገዳው የአሜሪካን ሉዓላዊነትና የሃገሪቱን መንግስት ደህንነት ማረጋገጥና ማስጠበቅ አላማ እንዳለው ተገልጿል።

በዚህም የኔትዎርክ ሲስተሙንና አሰራሩን ከመረጃ መረብ ደህንነት ስጋት ነጻ የማድረግ እቅድ አለውም ነው የተባለው።

ብሉምበርግ ካስፐርስኪ ከተቋማዊ ስራ ይልቅ ከሩሲያው የደህንነት ተቋም ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው መረጃዎችን በመጥቀስ ዘግቧል።

በዚህም መንግስታዊ መረጃዎችን በመጥለፍ እና በመሰለል ለደህንነት ተቋሙ ያቀርባል የሚል ግምት እንዳለም ነው መረጃው የሚጠቅሰው።

የሞስኮው ኩባንያ በበኩሉ ከደህንነት ተቋሙ ጋር አለህ የተባለው ግንኙነት በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል ብሏል።

በሩሲያ ከመረጃ መረብ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ጥቃቶች፥ መረጃ መረብ በርባሪዎቹ የሚታወቁበትንን አልያም የሚለዩበትን መንገድ ከማመቻቸት የዘለለ ድጋፍ እንደማያደርግም ገልጿል።

ከዚህ ባለፈ ግን ተቋሙ በተባለው ደረጃ ከመንግስትና ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ከመረጃ መረብ ስለላ ጋር በተያያዘ ግንኙነት የለኝም ብሏል።

ተቋሙ አለም ላይ በመረጃ መረብ ደህንነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከመዋጋት በዘለለም የቀረበበትን አይነት ውንጀላ ውስጥ ተሳትፎ እንደማያደርግም ነው የገለጸው።

ያም ሆነ ይህ ግን የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በተቋሙ ላይ በጣለው እገዳ የካስፐርስኪ አገልግሎት በአሜሪካ የሚቆም ይሆናል።

 

 

 


ምንጭ፦ www.techworm.net