ፈረንሳይ በጎግል ላይ የጣለችው ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ የታክስ ቅጣት ተሻረ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 7፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)የፈረንሳይ የግብር አስተዳደር በጎግል ላይ የጣለው የ1 ነጥብ 27 ቢሊየን ዶላር የታክስ ቅጣት በሀገሪቱ ፍርድ ቤት ተሻረ፡፡

ጎግል ፈረንሳይ ለሚገኙ ኩባንያዎች ምርት እና አገልግሎታቸውን በኢንተርኔት እንዲያስተዋውቁ በደንበኛነት ከመዘገባቸው በኋላ ከገቢው ውስጥ ግብር አልከፈለም በሚል ነው ቅጣቱ የተጣለበት፡፡

ሆኖም የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ጎግል ኩባንየዎቹን የማስታወቂያ ውል ያስፈረማቸው አየርላንድ በሚገኘው ቅርንጫፉ አማካኝነት በመሆኑ እንዲሁም በፈረንሳይ ቋሚ መቀመጫ ስለሌለው ቅጣቱን የመክፈል ህጋዊ መሰረት የለውም የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በፈረንሳይ የሚገኘው የጎግል ቅርንጫፍም ይህን ስራ የሚሰራ የሰው ሃይል የሌለው በመሆኑ ቅጣቱ ተገቢ አይደለም ሲል ወስኗል ፍርድ ቤቱ፡፡

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የፈረንሳይ መንግስት ይግባኝ መጠየቅ ይችላል ተብሏል፡፡

ጎግል የአውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹን በአየርላንድ ብቻ በመክፈት ሊጣልበት የሚችለውን የታክስ መጠን በመቀነስ ይታወቃል፡፡

ይህም ኩባንያው የሚያገኘውን ገቢ እና የትርፍ መጠን የማሳደጊያ ስትራቴጂ አንዱ አካል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ጎግል በቅርቡ ከታክስ አስተዳደር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ለጣሊያን 306 ሚሊየን ዩሮ፣ ለእንግሊዝ ደግሞ 130 ሚሊየን ዩሮ ለመክፈል መስማማቱ አይዘነጋም፡፡

ከጎግል በተጨማሪ ፌስቡክ እና አማዞን ኩባንያዎች በታክስ ክፍያ ማጭበርበር ትችት ይቀርብባቸዋል።

 

 


ምንጭ፡- አሶሼትድ ፕሬስ