ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ሰባት አደገኛ የሳይበር ጥቃቶች..

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 6፣ 20069 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርብ አመታት ውስጥ በተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች ሆስፒታሎች፣ የባቡር ጣቢያዎች፣ የኒዩክሌር ሀይል ማመንጫዎች እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የግል የንግድ ተቋማት ተጠቂ መሆናቸው ይታወቃል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ እና 2000 መጀመሪያ አካባቢ ከተዛመቱ የኮምፒውተር ቫይረሶች በበለጠ ከቅርብ አመታት ወዲህ የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች እጅግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።

የኢንተርኔት መስፋፋት የመረጃ ጠላፊዎች የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በፍጥነት እንዲያሰራጩ እና በጣም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን እንዲመዘብሩ አስችሏል።

በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት የሳይበር ጥቃቶች በታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ መሆናቸው ይነገራል።

ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ዋነክራይ (WannaCry)

በዚህ አመት ከተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች ሁሉ በርካቶችን ያነጋገረው ዋነክራይ ነው።

በዋናነት የማይክሮሶፍት ያልተሻሻሉ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞችን የሚጠቀሙ ኮምፒውተሮችን ኢላማ ያደረገው ጥቃት ከ150 በላይ ሀገራት የሚገኙ ከ230 ሺህ በላይ መሳሪያዎችን አጥቅቷል።

በዚህ የሳይበር ጥቃት በብሪታንያ ሆስፒታሎች፣ በጀርመን የባቡር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች፣ በስፔን ደግሞ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አቅራቢዎች ተጠቂ ሆነዋል።

አብዛኞቹ የዋነክራይ ተጠቂዎች የማይክሮሶፍት ኦፕሬቲንግ ሲስተም በማሻሻል (አፕዴት በማድረግ) እና ጠንካራ የኢንተርኔት ደህንነት ሶፍትዌሮችን በመጫን ጉዳት ሳይደርስባቸው ከጥቃቱ አምልጠዋል።

ሻሞን ወይንም ዲስትራክት (Shamoon or Disttrack)

ከኢነርጂ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ተቋማትን ለማጥቃት የተሰራው የኮምፒውተር ቫይረስ ሻሞን፥ በ2012 ነበር የተሰራጨው።

“Cutting Swords of Justice” በተሰኘ የመረጃ መንታፊ ቡድን የተለቀቀው ይህ ቫይረስ በመካከለኛው ምስራቅ የኢነርጂ ልማት ግዙፍ ኩባንያ የሆነውን የሳዑዲ አማርኮ ኩባንያ የመረጃ ስርአት ለማጥፋት ነው ኢላማ ያደረገው።

ቫይረሱ 30 ሺህ በሚሆኑ የኩባንያው ኮምፒውተሮች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ ኮምፒውተሮቹ ከኢንተርኔት ጋር እንዳይገናኙ እና እርስ በርስ እንዳይተሳሰሩ አድርጓል።

ጥቃቱ የኳታሩ ራስ ጋዝ ኩባንያ እና የአውስትራሊያውን ኤል ኤን ጂ ኩባንያ የመረጃ ስርአት ላይ ጉዳት አድርሷል።

ስቱክስኔት

በፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የስልጣን ጊዜ መገባደጃ ላይ የአሜሪካ መንግስት የኢራን የኒዩክሌር ጦር ማብለያ ጣቢያዎች ላይ የሳይበር ጥቃት ለማድረስ ሞክሯል።

ዋሽንግተን ከእስራኤል ጋር በመሆን ስቱክስኔት የተሰኘ ቫይረስ ሰርታለች።

ቫይረሱ የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያዎች መሳሪያዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነበር የተሰራው።

ስቱክስኔት ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን፥ በአንድ የኢራን የኒዩክሌር ማብለያ ጣቢያ ብቻ ከ1 ሺህ በላይ የኒዩክሌር ማብለያዎች (centrifuges) ስራ እንዲያቆሙ አድርጓል።

ይህ የሳይበር ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ነው የኮምፒውተር ደህንነት ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ኦፕሬሽን ሻዲ ራት (Operation Shady RAT)

እንደ አውሮፓውያኑ በ2008ም በ14 ሀገራት በሚገኙ የመንግስት እና የግል ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተፈፅሟል።

በተከታታይ በተፈፀሙ ተመሳሳይ የሳይበር ጥቃቶች በተለያዩ ሀገራት ጉዳት መድረሱን ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።

የሳይበር ጥቃቱ ምንጭ እስካሁን እየተጣራ ሲሆን፥ የቻይና መንግስት ከዚህ ዘመቻ ጀርባ እንደሚኖር ተገምቷል።

ቲታን ሬን (Titan Rain)

በአውሮፓውያኑ 2000 መግቢያ የአሜሪካ የኮምፒውተር ስርአቶች ያልተለመደ ችግር ገጥሟቸው ነበር።

ከሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር የሚሰሩ ተቋማትም ከፍተኛ የመረጃ ዘረፋ አጋጥሟቸዋል።

ጥቃቱ ለሶስት አመታት የዘለቀ ሲሆን፥ ዋሽንግተን ከጥቃቱ ጀርባ ቻይና እንዳለችበት ትወቅሳለች።

የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ ጥቃት የደረሰበት ቢሆንም እንደ አሜሪካ የበረታ አልነበረም ተብሏል።

ኦፕእስራኤል (OpIsrael)

በ2013 የእስራኤላዊያን እልቂት በሚታሰብበት ዕለት የተጀመረው ፀረ እስራኤል የሳይበር ጥቃት በርካታ የእስራኤል ድረ ገፆችን ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጓል።

በዚህ ጥቃት የድረገፆች የመረጃ ቋት የተመዘበረ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቶች፣ ጋዜጦች፣ የንግድ ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ባንኮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የጥቃቱ አድራሾች ዋና አላማም በእስራኤል ደስተኛ አለመሆናቸውን ማሳየት እንደነበር ተገልጿል።

በሀምሌ 2009 የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች

እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 ሀምሌ ወር ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካን ኢላማ አድርገው በተቃጡ የሳይበር ጥቃቶች ከ100 ሺህ በላይ ኮምፒውተሮች ተጠቅተዋል።

በዚህ ጥቃት ዋይት ሀውስ፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የደቡብ ኮሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ድረ ገፆች ኢላማ ተደርገዋል።

እስካሁን የጥቃቱ መነሻ እና አላማ በግልፅ አልታወቀም።

ይሁን እንጂ በርካታ ባለሙያዎች የሰሜን ኮሪያ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴር ለጥቃቱ ተጠያቂ መሆኑን ይገልፃሉ።

 

 

 

ምንጭ፦ www.techworm.net/

 

 

 


በፋሲካው ታደሰ