ኬንያ አሽከርካሪዎች ዲጂታል የመንጃ ፈቃድ እንዲጠቀሙ ልታስገድድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኬንያ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን እየሰራች መሆኗን ገልጻለች።

በሀገሪቱ የሚደርሱ የትራፊክ ደንብ ጥሰቶችን እና የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የዲጂታል የመንጃ ፍቃድ እንዲኖራቸው ልታደርግ መሆኑንም አስታውቃለች።

የሀገሪቱ የትራንስፖርት ደህንነት ባለስልጣንበ በአሁኑ ወቅት 100 ሺህ ስማርት የመንጃ ፍቃድ ካርዶችን ዝግጁ ማድረጉን አስታውቋል።

ይህ ዲጂታል የመንጃ ፍቃድ ካርድ አሽከርካሪው አደጋ ሲያደርስ ለሚመለከተው አካል የሚያሳውቅ የቴክሎጂ ክፍል ተገጥሞለታል ነው የተባለው።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስም ደንብ የሚጥሱ አሽከርካሪዎች ነጥብ እንዲቀነስባቸው ከማድረግ የመንጃ ፍቃዱን እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድም ዝግጅት ማድረጉን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የማሽከርከር ብቃታቸውን በየጊዜው እንዲያሻሽሉ በየጊዜው ስልጠና መውሰድ አለባቸው ብሏል።

በስማርት መንጃ ፍቃዱ ላይ የአሽከርካሪዎቹ ዝርዝር መረጃ እና ፎቶ ግራፍ ይካተታል ተብሏል።

ካርዱ 20 ነጥቦች የሚይዝ ሲሆን፥ አደጋ በሚያርሱበት ጊዜ የሚቀንስ ይሆናል፤ ለአብነትም ደርቦ ማሽከርከር 1 ነጥብ ያስቀንሳል።

ጠጥቶ ማሻከርከር እና በፍጥነት ማሽከርከር የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች ደግሞ ከ10 ነጥብ በላይ መቀነስ፣ የገንዘብ ቅጣት እና ሌሎች የዲሲፕሊን እርምጃዎችን ጨምሮ መንጃ ፍቃዱን እስከ ህይወት ፍጻሜ እንዳያገኙ የማድረግ እርምጃ ያስወስዳል።

ባለስልጣኑ በግዴለሽነት አደጋ የሚያደርሱ እና የትራክ ደንቦችን ሆን ብለው ጥሰው አደጋ የሚጋጥማቸውን አሽከርካሪዎች፥ ለመድህን ኩባንያዎች አደገኛ ደንበኞች እንደሆኑ አሳውቃለሁ ብሏል፡፡

ስማርት የመንጃ ፍቃዱን የኬንያ ብሔራዊ ባንክ በ2 ነጥብ 1 ቢሊየን የኬንያ ሽልንግ ወይም ከ20 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እያመረተ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ3 ሚሊየን በላይ አሽከርካሪዎች በትራንስፖርት ደህንነት ባለስልጣን ዳታቤዝ ተመዝግበዋል።

ኬንያ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ሁሉም የሀገሪቱ አሽከርካሪዎች ዲጂታል ስማርት የመንጃ ፍቃድ እንዲይዙ አልማለች።

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-ሲ ጅ ቲ ኤን