ኢንስታግራም ከማህበራዊ የትስስር ገጾች ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ምክንያት በመሆን ቀዳሚ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንግሊዝ የተሰራ አንድ የዳሰሳ ጥናት ከማህበራዊ የትስስር ገፆች ውስጥ ለወጣቶች የአዕምሮ ጤና ቀውስ ኢንስታግራምን የሚያክል የለም ብሏል።

በዓለማችን ውስጥ 90 በመቶ ወጣት ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል በበለጠ የማህበራዊ የትስስር ገፅን ይጠቀማል፡፡

ጥናቱ እድሜያቸው ከ14 እስከ 24 የሚሆኑ 1 ሺህ 479 ሰዎችን መጠይቅ አድርጓል፡፡

በመጠይቁ ውስጥም ከአምስት የማህበራዊ ትስስር ገፆች መካከል የትኛው የበለጠ አዕምሯዊ ቀውስ እንደሚፈጥርባቸው ምላሽ እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡

በተለይም እያንዳንዱን የማህበራዊ ትስስር ጭንቀትን፣ ድብርትን፣ ብቸኝነትን እና አካላዊ መደንዘዝን ከመፍጠር አኳያ በደረጃ እንዲስቀምጡም ተደርጓል፡፡

instagram_collection.jpg

የዳሰሳ ጥናቱ ከዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ፌስቡክ እና ትዊተር የማህበራዊ የትስስር ገፆች ውስጥ በጤናቸው እና ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ያለውን በደረጃ እንዲያስቀምጡ ነው ያደረገው፡፡

ዩቲዩብ ትዊተር እና ፌስቡክን በማስከተል በአዕምሮ ጤና ላይ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖ የማይፈጥር በሚል በቀዳሚ ደረጃ ላይ ሰፍሯል፡፡

ኢንስታግራም ለማህበራዊ ህይወት እና ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ምክንያት በመሆን ቀዳሚ ሲሆን፥ ስናፕቻት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

instagrammmmm.jpg

በአዕምሮ ጤና ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችም የማህበራዊ ትስስር ገፅ ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎቻቸውን በአዕምሮ ጤና ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው ጉዳት እና ስለአጠቃቀሙ ወሰን ሊያሳውቁ እንደሚገባ እየጎተጎቱ ነው፡፡

እንደ ኢንስታግራም ያሉ የማህበራዊ የትስስር ገፆች በወጣቶች የአዕምሮ መታወክን በመፍጠር አምራች ትውልድን እንዳያሳጡም ስጋት ፈጥሯል፡፡

በመሆኑም የማህበራዊ ትስስር ገጽ የሚያበለፅጉ ኩባንያዎች መተግበሪያዎቻቸውን ከጥቅማቸው ባሻገር ጉዳታቸው እንዳያመዝን በንቃት መስራት አለባቸውም ተብሏል፡፡

 

 

 

 

 

ምንጭ፡- ቢቢሲ