የማይክሮሶፍት እና ጎግልን የመረጃ መረብ ሰብሮ የገባው የ13 ዓመት ታዳጊ ይናገራል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) 13 አመት ታዳጊ ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ ተብሎ ቢጠየቅ “ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ አውሮፕላን አብራሪ አልያም የጠፈር ተመራማሪ” የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ይህ ፓኪስታናዊ ግን የመረጃ መንታፊ መሆን እንደሚፈልግ አስታውቋል፤ ይሁን እንጂ ምግባረ መልካም የመረጃ መንታፊ መሆን ነው ፍላጎቴ ብሏል።

አህሳን ታሂር የተባለው ታዳጊ በፓኪስታን ካራቺ ነው የሚኖረው።

ታሂር በሰራቸው መተግበሪያዎችም ሆነ በሌሎች ኩባንያዎች በርካታ የደህንነት ችግሮች እንደሚያስተውል ይናገራል።

ታዳጊው ወደ የሳይበር ደህንነት ስራ የተቀላቀለውም የግል ድረ ገጹ በመረጃ መንታፊዎች ሲጠቃ እንደነበር ያስታውሳል።

በዩትዩብ ቪዲዮዎችን በመመልከት፣ የመረጃ መረብ ስርቆትን የተመለከቱ ፅሁፎችን በማንበብ እና ያወቀውን ወደ ተግባር ለመቀየር በመሞከር ነው ታዳጊው ራሱን ብቁ የደህነነት አማካሪ ያደረገው። 

ታሂር የመረጃ መረብ ስርአት ሰብሮ የመግባት ችሎታውን ተጠቅሞ የተለያዩ ተቋማትን ድረ ገፆች በመፈተሽና ለመረጃ ስርቆት ያላቸውን ተጋላጭነት በማሳወቅ ገንዘብ ማግኘት ጀምሯል።

ታዳጊው ማይክሮሶፍት፣ ጎግል እና ኡበርን ጨምሮ የተለያዩ ኩባንያዎችን የመረጃ መረብ ስርአት ሰብሮ መግባት ችሏል።

በሌሎች ተቋማትም በኮምፒውተር ፕሮግራም አልያም ስርአት ውስጥ ስህተት እንዲፈጠር የሚያደርጉ “በግስ” የተሰኙ ኮምፒውተሮችን የሚያንቀራፍፉ ነገሮች እንዲፈልግ ተቀጥሯል።

“በርካታ መረጃ መንታፊዎች ቢኖሩ የበዙ “በግስ” እንደሚገኙ እርግጥ ነው፤ ይህም የኩባንያዎችን የሳይበር ደህነነት ለማረጋገጥ ይረዳል” ብሏል ታዳጊው።

እኩዮቹ የልጅነት ጊዜያቸውን በመዝናናት ሲያሳልፉ “በግስ” በመፈለግ ገንዘብ ማግኘትን የመረጠው ፓኪስታናዊ፥ የሶፍትዌር ኢንጂነር መሆን የሚፈልግ ሲሆን የራሱን ኩባንያ አቋቁሟል።

ታዳጊው በዚሁ ስራው አማካኝነት ባገኘው ገንዘብ የአይፎን 7 ስልክ የገዛ ሲሆን፥ 18 አመት ሲሞላው የራሱን ተሽከርካሪ ለመግዛት ገንዘብ እያጠራቀመ ነው።

አህሳን ታሂር በቀጣይም የበርካታ ታላላቅ ኩባንያዎችን የመረጃ መረብ ሰብሮ በመግባት የአደጋ ተጋላጭነታቸውን በማጥናት የደህንነት ደረጃቸውን ማሳወቅ እንደሚፈልግ ገልጿል።

 

ምንጭ፦ www.nbcnews.com/