ሳምሰንግ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ5 ሚሊየን በላይ የኤስ 8 ስልኮችን መሸጡን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)ሳምሰንግ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ5 ሚሊየን በላይ የኤስ 8 እና ኤስ 8 ፕላስ ስልኮችን መሸጡን ይፋ አደርጓል፡፡

ኩባንያው ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 21 ጀምሮ በተወሰኑ ሀገራት ብቻ ባደረገው የሙከራ ሽያጭ የሸጠው የስልክ ብዛት እንደ አዲስነቱ ጥሩ የሚባል መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከሁለቱ ስልኮች የስልክ አይነቶች በብዛት የተሸጠው ገና ባይጣራም፥ በዋጋው ቅናሽ መሆን እና በዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ ምክንያት ኤስ 8 የተሻለ በብዛት ሊሸጥ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥም ከሀገራት እና ከተቋማት የቀረበለት የቅድሚያ የግዥ ትዕዛዝ፥ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ30 በመቶ ጨምሯል፡፡

በሌላ በኩል አፕል ኩባንያ 50 ነጥብ 8 ሚሊየን የአይፎን 7 እና አይፎን 7 ፕላስ ስልኮቹን በአንድ ሩብ ዓመት ውስጥ መሸጡ የተነገረ ሲሆን፥ በአማካይ 16 ነጥብ 9 ሚሊየን ስልክ በየወሩ መሸጡም ተጠቁሟል፡፡

አሁን ላይ ከሳምሰንግ እና ከአፕል ኩባንያ በስልክ ሽያጭ ቀዳሚውን ለመለየት ከባድ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

ሳምሰንግ ባፈው ዓመት በኤስ 7 ስልኩ የባትሪ ችግር ያጋጠመውን ቀውስ በኤስ 8 እና ኤስ 8 ፕላስ ስልኮቹ ሽያጭ እንደሚያካክስም ይጠበቃል፡፡

በተለይም የሳምሰንግ ኤስ 8 ስልክ በመላው ዓለም ሽያጩ ሲጀመር፥ ቀዳሚ ሊያደርገው እንደሚችል ነው የተጠቆመው፡፡

www.engadget.com