ዩ ትዩብ ሀሰተኛ ዜናዎችን ለመከላከል ያለመ አውደ ጥናት ለታዳጊዎች አዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዩ ትዩብ የኢንተርኔት ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ ሀሰተኛ ዜናን ለመከላከል ያለመ የቪዲዮ ስርጭት ንቅናቄ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው እድሜቸው ከ13 እስከ 18 ዓት ለሚሆኑ እንግሊዛውያን ታዳጊዎች አውደ ጥናት አዘጋጅቷል፡፡

ይህ አውደ ጥናትም የኢንተርኔት ዜጎች ቀንን በማስመልከት የሚዘጋጅ ሲሆን፥ በሁነቱ ላይ ስለ ንግግር ነጻነት፣ የሰለጠነ እና ገንቢ አስተያየት ስለመስጠት፣ እንዲሁም በቀጥታ ኢንተርኔት ላይ ስለሚደርሱ ትንኮሳዎች አስከፊነት ማብራሪያዎች ቀርቡበታል፡፡

ዩቲዩብ በቅርቡ የጥላቻ ንግግሮችን በማስተናገዱ እና ሳይቆጣጠራቸው በመቅረቱ ወቀሳ በርትቶበታል፡፡

ባለፈው ወርም የእንግሊዝ መንግስት በዩቲዩብ የሚያስኬደውን ማስታወቂያ ተገቢ ባልሆነ ቪዲዮ ላይ እንዲተላለፍ በማድረጉ ከዩ ትዩብ እንዲነሳ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

የዩ ቲዩብ ባለቤት የበላይ የሆነው ጎግል ኩባንያም በቪዲዮ ማስተላለፊያ ድረ ገጹ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ እና አሰራሩን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የዩ ትዩብ የፐብሊክ ፖሊሲ ሃላፊ ናኦሚ ጉመር እንደተናገሩት ኢንተርኔት ሰዎች የሚያስገቡለትን ሁሉ መቀበሉ ለተለያዩ ቀውሶች ምክንያት ሆኗል፡፡

በሌላ በኩልም የምናውቀውን እውቀት፣ ተሞክሮ እና ምክር ለሌሎች ሰውች የምናስተላልፍበት መሆኑ ትልቁ ፋይዳው እና ዓላማው ነው ብለዋል፡፡

ስለ ዓለም ህዝብ መብት መከበር፣ ማንኛውም ሰው ተስፋ እንዲኖረው፣ አወንታዊ የሆኑ የተለያዩ ሀቀኛ መረጃዎችን ለመለዋወጥ መዋል እንደሚገባው የሚመክረው ዩቲዩብ

ታዋቂ ሰዎችን በአውደ ጥናቱ በማሳተፍ ለታዳጊዎቹ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ያድረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስካሁንም የአውደ ጥናቱ ልዩ የሙከራ ሁነቶች ተዘጋጅተው ስኬታማ በመሆናቸውን ነው መደበኛው አውደ ጥናት የተከፈተው፡፡

በተለይም ወጣቱ የዓለም ማህበረሰብ አብዛኘውን ጊዜውን በኢንተርኔት ላይ የሚያሳልፍ በመሆኑ አዎንታዊ የመረጃ ልውውጦችን እንዲደርጉ ከማገዝ ባሻገር አሉታዊ እና ጥላቻን የሚሰብኩ መረጃዎችን እንዳይቀበሏቸው ማስገንዘብ ተገቢ ነው ተብሏል፡፡

 

ምንጭ፡- ቢቢሲ

በምህረት አንዱዓለም