ፌስቡክ በአእምሮ ትእዛዝ ብቻ ኮምፒውተር ላይ መፃፍና መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፌስቡክ ያለምንም የእጅ ንክኪ ኮምፒውረታችንን በአእምሯችን ብቻ ለማዘዝ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ኩባንያው በመስራት ላይ የሚገኘው ሶፍትዌር “ሳይለንት ስፒች (silent speech)” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፥ በአንድ ደቂቃም እስከ 100 ቃላትን ለመፃፍ የሚያስችል መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል።

“የሳይለንት ስፒች” ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ያለው ፌስቡክ፥ የሰዎችን አእምሮ ለማምነብ የሚያስችለው አዲስ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልገውም ገልጿል።

እንደ ፌስቡክ ገለፃ፥ ቴክኖሎጂው ሁሉንም የምናስባቸውን ነገሮች ወደ ጽሁፍነት አይቀይርም፤ ወደ ፅሁፍ እንዲቀየር የምንፈልገውን ነገር ብቻ በመምረጥ መቀየር እንችላለን።

የፌስቡክ ኩባንያ መስራች እና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ፥ “አዲስ እየሰራን ያለነው ቴክኖሎጂ በአእምሯችን ውስጥ ያለውን ነገር አውጥተን ለመፃፍ የሚረዳን ነው” ብሏል።

ሶፍትዌሩ አሁን በስልካችን ላይ ስንፅፍ ከሚወስድብን ጊዜ በአምስት እጥፍ እንደሚፈጥንም ማርክ ዙከርበርግ አስታውቋል።

ቴክኖሎጂውንም በአካላችን ላይ በሚደረግ አሊያም በሚለበስ መልኩ እንደሚሰራም ነው የተናገረው።

አዲሱ “ሳይለንት ስፒች” ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች እጅ ከመድረሱ በፊትም ረቀቅ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደሚካተቱበት ዙከርበርግ አስታውቋል።

ቴክኖሎጂው መቼ ሙሉ በሙሉ ተመርቶ ገበያ ላይ ይውላል በሚለው ዙሪያ ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ምንጭ፦ www.bbc.com/news