ቨሪዞን ከ1 ቢለየን ዶላር በላይ በሆነ ወጭ ኦፕቲካል ፋይበር ለመግዛት ተስማምቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቨሪዞን ኮሙኒኬሽንስ ኩባንያ የ1 ነጥብ 05 ቢለየን ዶላር ኦፕቲካል ፋይበር ከኮርኒንግ ኩባንያ ለመግዛት ስምምነት ፈርሟል፡፡

የአሜሪካ ግዙፍ የገመድ አልባ ኔትወርክ አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ቨሪዞን የኔትወርክ መሰረተ ልማቱን ለማሻሻል አቅዷል ተብሏል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ኮርኒንግ ከፈረንጆች 2018 እስከ 2020 ድረስ በየዓመቱ 12 ነጥብ 4 ሚሊየን ማይል ርዝመት ያለው ኦፕቲካል ፋይበር ለቨሪዞን የሚሸጥለት ይሆናል፡፡

ለዚህም 1 ነጥብ 05 ቢለየን የአሜሪካ ዶላር ክፍያ ከቨሪዞን ያገኛል፡፡

ቨሪዞን፥ ፋይበር ለቀጣዩ ወይም ለአምስተኛው ትውልድ በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡

ኩባንያው ከኤሪክሰን የኔትወርክ መሳሪያ አምራች ኩባንያ ጋር በመሆን አምስተኛ ትውልድ የደረሱ መደበኛ የገመድ አልባ የኔትወርክ አገልግሎቶችን በአሜሪካ 11 ገበያዎች ላይ ሙከራ አድርጓል፡፡

ይፋዊ ሽያጩንም በ2018 በይፋ እንደሚጀምር ተጠቁሟል፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-ሬውተርስ