የማሌዥያ አየር መንገድ በሳተላይት አማካኝነት አውሮፕላኖቹን በመቆጣጠር የመጀመሪያው ሊሆን ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹ በዓለም አፅናፍ ሁሉ አቆራርጠው ጉዞ ሲያደርጉ በሳተላይት አማካኝነት ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ፈርሟል፡፡

በዚህም ባልተጠበቀ ሁኔታ በሳተላይት አማካኝነት የአውሮፕላኖቹን ጉዞ የሚቆጣጠር የመጀመሪያው የንግድ አየር መንገድ ይሆናል ተብሏል፡፡

ማሌዥያ አየር መንገድ ከአይሬኦን፣ ሲታ ኦንአየር እና ከፍላይት አዌር ጋር የኔትዎርክ ሳተላይቶችን ለመጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡

የኔትወርክ ሳተላይቶችን መጠቀሙ በጠረፋማ እና በዓለም የዋልታ በረዷማ ስፍራዎች ሁሉ የአውሮፕላኖቹን የጉዞ ደህንነነት ለማረጋገጥ ያስችለዋል እየተባለ ነው፡፡

በፈረንጆች 2014 ኤም ኤች 370 አውሮፕላን 239 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ድንገት የገባበት ከጠፋ ወዲህ የበረራ ኢንዱስትሪው ልዩ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ላለፉት ዓመታትም የኤም ኤች 370 አውሮፕላን መጥፋት በእንቆቅልሽነት የቀጠለ ሲሆን፥ ጥቂት የሳተላይት ምስሎች ግን በህንድ ውቅኖስ መከስከሱን ያረጋግጣሉ፡፡

ባህር ጠላቂ ፈላጊዎችም የአውሮፕላሉን አሻራ እየፈለጉ ሲሆን፥ በዚህ ዓመት መጨረሻም የማሌዥያ መንግስት ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ጠበቃል፡፡

የሰሞኑ የድርጅቱ እቅድም ከዚህ ዓይነቱ አደጋ ራሱን ለመከላከል እና የተጓዦቹን እና የአውሮፕላኖቹን የበረራ ደህንነት ለመቆጣጠር እና ለማረጋገጥ ነው ተብሏል፡፡

ሌሎች አየር መንገዶችም ይህን ፈለግ እንዲከተሉ በበረራ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-www.ibtimes.co.uk