አፕል ባለ 10 ነጥብ 5 ኢንች ስፋት ያለው አይፓድ ለገበያ ሊያቀርብ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ግዙፉ ሞባይል አምራች ኩባንያ አፕል አዲስ አይፓድ ለገበያ ሊያቀርብ መሆኑ ተሰምቷል።

አፕል ለገበያ የሚያቀርበው አይፓድ ዘመናዊ ሲሆን፥ በመጠኑ አነስ ብሎ የተሻለ ስክሪን ስፋት እንዳለው ተገልጿል።

አዲሱ አይፓድ 10 ነጥብ 5 ኢንች የስክሪን ስፋት ሲኖረው፥ የአይፓዱ አጠቃላይ መጠን ኩባንያው ከዚህ ቀደም ለገበያ ካቀረበው የባለ 9 ነጥብ 7 ኢንች ስክሪን ስፋት እኩል ነው ተብሏል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለጹት አዲሱ አይፓድ በመጠን አነስተኛ ሆኖ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

አዲሱ አይፓድ ተጠቃሚዎች መገልገል የሚችሉበትን ስማርት ኪቦርድ ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

ይህ መሆኑ ደግሞ አይፓዱን በፈለጉት ጊዜ እና ቦታ መገልገል ያስችላቸዋል።

ዋጋው ምናልባትም እስከ 600 የአሜሪካ ዶላር ሊደርስ ይችላል ነው የተባለው።

አይፓዱ ገመድ አልባ ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችል ሲሆን፥ ቢበዛ እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ ለገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ዘመናዊ እና ጥርት ያለ ስፒከር ያለው ሲሆን፥ ጥርት ያለ ምስል ማስቀረት የሚያስችል ካሜራ እና በስክሪኑ ላይ ያለ ኪቦርድ በእርሳስ መገልገል ያስችላልም ተብሏል።


ምንጭ፦ gadgetsnow.com