ሩሲያ ሰላዮቼ በያሁ ድረ ገጽ ጠለፋ ላይ አልተሳተፉም አለች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ክሬምሊን የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የሩሲያው የስለላ ተቋም ኤፍ.ኤስ.ቢ ሰላዮች በያሁ ድረ ገፅ ጠለፋ ላይ ተሳትፈዋል ብሎ ያቀረበውን ውንጀላ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡

የአሜሪካው የፍትሕ ቢሮ ረቡዕ ዕለት ባሰማው ክስ ሁለት የኤፍ.ኤስ.ቢ ሰላዮችን የያሁ ድረ ገፅን በመጥለፍ በደንበኞቹ ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ውንጀላ አቅርቦ ነበር፡፡

ክሱም አሜሪካ የሩሲያን ባለስልጣናት ለመጀመሪያ ጊዜ የወነጀለችበት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡

ያሁ በ2014 መስከረም ወር ከ500 ሚሊየን የሚሆኑ ደንበኞቹ አድራሻ መበርበሩ ይታወቃል፡፡

ታዲያ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔሽኮቭ ሁል ጊዜ እንደምንለው የሩሲያ መንግስትም ሆነ የሩሲያ የስለላ ተቋማት በአስነዋሪ እና ህገወጥ የሳይበር ጥቃት አልተሳተፉም፤ ወደፊትም አይሳተፉም ብለዋል፡፡

አሁን የፍትሕ ቢሮው ያቀረበው ውንጀላም መሰረተቢስ ነው ብለውታል፡፡

አሜሪካ በያሁ ድረ ገፅ ጠለፋ የጠቀሰቻቸው ሁለቱ የሩሲያ ሰላዮች ድሚትሪ ዶኩቻቭ እና ኢጎር ሱቺን ናቸው፡፡

የሳይበር ጥቃቱን የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍ.ቢ.አይ ለሶስት ዓመታት በጥብቅ ከሚፈልጋቸው ካሪም ባራቶቭ እና አሌክሲ ቤላን ጋር እንደፈፀሙት ጠቅሳለች፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ