ከ48 ሚሊየን በላይ የትዊተር አድራሻዎች የሰዎች ሳይሆኑ የሶፍትዌር ፕሮግራም ናቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአጠቃላይ የትዊተር አድራሻዎች ውስጥ ከ48 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት የሰዎች ሳይሆኑ ሶፍትዌር ፕሮግራሞች መሆናቸውን አንድ ጥናት አመላከተ።

እነዚህ በትዊተር ማንኛውም ሰው የሚያደርገውን ሁሉ እንዲያደርጉ የተሰሩ የሶፍትዌር ፕሮግራሞች “Bots” ይሰኛሉ።

ከትዊተር አድራሻዎች (አካውንት)15 በመቶን የሚይዙት እነዚህ የሶፍትዌር ፕሮግራሞች (“Bots”)፥ ሌሎች አካውንቶችን የሚከተሉ (ፎሎው የሚያደርጉ) ሲሆን አንዳንድ መልዕክቶችንም ሪትዊት ያደርጋሉ።

በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በተደረገ ጥናት ከ9 እስከ 15 በመቶ ንቁ የትዊተር ተጠቃሚዎች የሶፍትዌር ፕሮግራሞች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ትዊተር በአሁኑ ወቅት 319 ሚሊየን ወርሃዊ ንቁ ተጠቃሚዎች አሉት፤ ከእነዚህም ውስጥ ከ48 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት የትዊተር አድራሻ ያላቸው ተጠቃሚዎች ሰዎች ሳይሆኑ የሶፍትዌር ፕሮግራም ናቸው ተብሏል።

የትዊተር ቃል አቀባይ ለሲኤንቢሲ እንደገለጹት፥ እነዚህ የሰፍትዌር ፕሮግራሞች (ቡትስ) ምንም እንኳን ከአሉታዊ ነገሮች ጋር ቢያያዙም በርካታ የቡትስ አድራሻዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ በመጠቆም እና የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥን የተመለከቱ ጥናቶችን ለማድረግ ያግዛሉ።

አንዳንድ ቡት አድራሻዎች ከመረጃ ምንተፋ ጋር ይገናኛሉ፤ አብዛኞቹ ግን ዜና እና መረጃዎች በፍጥነት ወደ ተጠቃሚዎች እንዲደርሱ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ትዊተር ባለፈው የካቲት ወር ከ8 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ተጠቃሚዎቹ ሰዎች አለመሆናቸውን መግለፁ ይታወሳል።

 

 

ምንጭ፦ www.techworm.net/

 

 


በፋሲካው ታደሰ