ኔዘርላንድስ በመንገድ ላይ ስማርት ስልክ እየተጠቀሙ ለሚጓዙ እግረኞች ልዩ የመንገድ መብራት ልትተክል ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኔዘርላንድስ ስማርት ስልካቸውን በደመነፍስ በመነካካት የሚጓዙ እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ ለማዳን ልዩ የመንገድ መብራትን በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ልታደርግ ነው።

በመንገዳቸው ላይ አንገታቸውን አቀርቅረው ስልኮቻቸውን በመነካካት መጓዝን ልማድ ያደረጉ እና ሱስ የሆነባቸው እግረኞች ለትራፊክ አደጋ እየተዳረጉ መምጣታቸው ችግር እየሆነ ነው ተብሏል።

ስማርት ስልካቸውን እየነካኩ መጓዝን ብቻ ትኩረት የሚሰጡ አብዛኛው እግረኞች ለተሽከርካሪ የትራፊክ አደጋ የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው።

እነዚህ ከስልካቸው ጋር የሚመሰጡ ሰዎች በራሳቸው ላይ ከሚደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ለሌሎች ሰዎች ጉዳት እና ሞትም ምክንያት እየሆኑ ነው ተብሏል።

ታዲያ ይህ ያሳሰባት ኔዘርላንዳዊ ቦደግራቨን ከተማ ደመነፍሳዊውን ተግባር መቆጣጠር እና መከላከል ሰዎችንም ከትራፊክ አደጋ ማዳን የሚያስችላትን ልዩ የመንገድ መብራት በመግጠም ሞክራለች።

መብራቱ ለሙከራ የተገጠመው በእግረኞች መንገድ ወለሉ ላይ ሲሆን፥ ይህም ከእይታቸው ጋር ቀጥታ እንዲገናኝ በማድረግ ከተመሰጡበት የስማርት ስልክ ለአፍታም ቢሆን ያነቃቸዋል ተብሏል።

ይህ ልዩ የመንገድ መብራትም በስልኮቻቸው ላይ አፍጥጠው ከኋላቸው እና ከፊታቸው የሚመጣን ተሸከርካሪ ልብ ለማይሉት እግረኞች መፍትሔ እንደሚሆን ነው የተገለጸው፡፡

ይህ ልዩ የመንገድ መብራት “+Lichtlijn” የሚባል ሲሆን፥ በሀገሪቱ በትራፊክ ጉዳዮች ላይ በሚሰራው የኤች አይ ጅ ድርጅት መሰራቱ ተነግሯል።

ይህ ስርዓት የተለያዩ ደማቅ ቀለም ያላቸው መብራቶችን ወደ እግረኞች ፊት ለፊት በማንጸባረቅ በጥልቅ የገቡበትን የስማርት ስልክ መነካካት ድርጊት እንዲያቆሙ ምልክት ይሰጣል ተብሏል።

በተለይም በመንገዶች ላይ ዋትስአፕ፣ የተለያዩ የስልክ ጨዋታዎች፣ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ሙዚቃ ማየት እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ያለማቋረጥ እየተጠቀሙ በእግር መጓዝ ከአደጋ አምጪ ሱሶች ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

የከተማዋ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ኬስ ኦስካም እንደተናገሩት፥ በልዩ የመንገድ መብራቱ የስማርት ስልክ መነካካት ልማዱን ለመለወጥ ቢከብድም አደጋውን መቀነስ ግን ይቻላል።

የኔዘርላንድስ የመንገድ ደህንነት ድርጅት ቃል አቀባይ ቨይሊግ ቨርኬር ኔደርላንድ በበኩላቸው አዲሱ ስርዓት መፍትሔ ሳይሆን፥ እግረኞች የሚያደርጉትን መጥፎ ተግባር ማበረታታት ነው በሚል ተቃራኒ ሀሳብ አቅርበዋል።

ምንም እንኳ የተለየ ቢሆንም ይህን መሰል የመንገድ የስማርት ስልክ ሱሰኞችን ከአደጋ የማዳኛ ስልት የቻይና እና አንዳንድ የጀርመን ከተሞችም ይጠቀሙበታል።

ምንጭ፡-https://www.techworm.net

በምህረት አንዱዓለም