እንግሊዝ የሳይበር ጥቃትን የሚከላከል ማዕከል ልትከፍት ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንግሊዝ መቀመጫውን በማዕከላዊ ለንደን ያደረገ የሳይበር ጥቃቶችን የሚከላከል ብሔራዊ ማዕከል ልትከፍት ነው፡፡

ማዕከሉን የሚከፍቱት ንግስቷ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

የኤፍ 5 ኔትዎርክስ የሲስተም ኢንጅነሪንግ ማናጀር ሚካኤል ብሮውን እንደተናገሩት፥ “ይህ ብሔራዊ የሳይበር ጥቃት መከላከያ ማዕከል ከሚሰራባቸው ተቋማት መካከል የሀገሪቱ የጤና ተቋም ዋነኛው ነው”።

ማዕከሉ የሀገሪቱ የስለላ ኤጀንሲ አንድ አካል መሆኑም የተጠቆመ ሲሆን፥ ባለፉት ሶስት ወራትም 188 የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉ ይፋ ሆኗል፡፡

ተቋማት የመረጃ ማደራጃ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎቻቸውን ከሳይበር ጥቃት የሚከላከሉ ስልቶችን መጠቀም እንዳለባቸውም ብራውን ተናግረዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት አድራሾች የመረጃ መጫኛ ሶፍትዌሮች ወይም መተግበሪያዎች ላይ መረጃዎችን የመዝረፍ እና የማጥፋት ትኩረት ስለሚያደርጉ ተቋማቱ ቅደመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት መከላከል አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የሳይበር ጥቃት ስጋቶችን መፈተሽ የሚችሉ ባለሙያዎችን፣ ከስርዓቱ ጋር የሚላመዱ ዘመናዊ አሰራሮችን መጠቀምም ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡- www.itproportal.com

በምህረት አንዱዓለም