ፌስ ቡክ በተንቀሳቃሽ ምስል መሃል የሚገቡ ማስታወቂያዎችን ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፌስ ቡክ በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መሃል የሚገቡ ማስታወቂያዎችን ሊጀምር ስለመሆኑ ገልጿል።

ኩባንያው ይህን የቪዲዮ መሃል ማስታወቂያ ለመሞከርም ዝግጅቱን ጨርሷል።

በገጹ ላይ የሚታዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከጀመሩ በኋላ መሃል ላይ የሚገቡት እነዚህ ማስታወቂያዎች ለተወሰኑ ሰከንዶች የሚቆዩ ናቸው።

ኩባንያውን በእነዚህ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አማካኝነት ገቢውን ለመጨመር ስለማሰቡም ገልጿል።

እነዚህ ማስታወቂያዎች በተመረጡና በብዛት ሊታዩ በሚችሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ይጀመራሉም ተብሏል።

የዘርፉ ተንታኞች ኩባንያው ይህን መሰሉን አገልግሎት መጀመሩ በዘርፉ ከተሰማሩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች አጋሮችን እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።

መሰል ማስታወቂያዎች የፌስ ቡክ ተከታታዮችን እንደማይረብሹም ተንታኞቹ ይገልጻሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የአገልግሎቱን ይዘት መወሰንና ረጅም ወይም አጭር የማድረግ ጉዳይ የኩባንያው ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።

ኩባንያው በገጹ የሚታዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ተቀባይነት በመጠቀም ከዚህ ዘርፍ የሚያገኝውን ገቢ እና ትርፍ የማሳደግ ፍላጎት እንዳለውም አስታውቋል።

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ