ያሆ ስሙን ሊቀይር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግዙፉ የኢንተርኔት መልዕክቶች መላላኪያ ያሆ ስሙን ወደ አልታባ ኮርፖሬሽን ሊቀይር መሆኑን አስታወቀ።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ማሪሳ ሜየርም ከስልጣናቸው ይነሳሉ ተብሏል።

ያሆ ከቨሪዞን ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ስምምነት ነው ስሙን እና ዋና ስራ አስፈፃሚውን የሚቀይረው።

ሌሎች አምስት የያሆ ዳይሬክተሮችም ከስልጣናቸው የሚነሱ ይሆናል።

ኩባንያው የዲጂታል ማስታወቂያ፣ ኢሜል እና ሌሎች ዋነኛ የኢንተርኔት ቢዝነሶቹን ለቨሪዞን በ4 ነጥብ 83 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመሸጥ መስማማቱ ይታወቃል።

ያሆ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ ላይ ከ500 ሚሊየን በላይ ደንበኞቹ የኢሜል አድራሻዎች ለመረጃ በርባሪዎች መጋለጣቸውን በሌላ ጊዜ ደግሞ 1 ቢሊየን የሚሆኑ ደንበኞቹ አድራሻ መሰረቁን ማስታወቁ አይዘነጋም።

ይህም ከቨሪዞን ጋር የተፈራረመውን ስምምነት እንዲከልስ ያስገድደዋል እየተባለ ነው።

የቨርዚን ስራ አስፈፃሚዎች ምንም እንኳን ከያሆ ጋር ስምምነት ላይ ብንደርስም የመረጃ ስርቆቱን ጉዳይ እያጣራን ነው ብለዋል።

ቀሪዎቹ የያሆ ዳይሬክተሮች በቻይናው አሊባባ ግሩፕ 15 በመቶ እንዲሁም በጃፓኑ ያሆ ኩባንያ 35 ነጥብ 5 በመቶ አክሲዮን ድርሻ የሚቋቋመው አልታባን ያስተዳድራሉ ተብሏል።

ኢሪክ ብራንት የአዲሱ ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።

 


በፋሲካው ታደሰ

android_ads__.jpg